ኮሮናቫይረስ፡ ወረርሽኝ የወለደው የአውሮፓ የብስክሌት አብዮት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከቡካሬስት እስከ ብራሰልስ፣ ከለንደን እስከ ሊዝበን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በመላው አውሮፓ በብስክሌቶች ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንት ብስክሌትን የመጠቀምን ባህልን በእጅጉ ከፍ አድርጎታል።
ወረርሽኙ ከጀመረ ወዲህ ብቻ በአውሮፓ ብስክሌቶች እና የብስክሌት መሰረተ ልማት ላይ አንድ ቢሊየን ዩሮ ወጪ የተደረገ ሲሆን ከዚህ በፊት ከነበረው በተጨማሪ 2300 ኪሎ ሜትር የብስክሌት መንገድም ተገንብቷል።
''በዚህ የወረርሽኝ ወቅት ከቦታ ለቦታ ለመንቀሳቀስ ብስክሌት መጋለብ የተሻለ አማራጭ ሆኖ ብቅ ብሏል'' ይላሉ መቀመጫውን ብራሰልስ ካደረገው የአውሮፓ የሳይክል ፌደሬሽን የመጡት ጂል ዋረን።
''ይህ ወረርሽኝ የብስክሌት ዘርፍ ምን ያክል ሊጓዝ እንደሚችልና ሕይወታችንን እንዴት መቃኘት እንዳለብን አሳይቶናል'' ይላሉ።
ለመሆኑ ለብስክሌት እና የብስክሌት መሰረተ ልማት ምን ያክል ወጪ ሆነ?
''ከዚህ በፊት ተጨማሪ የብስክሌት መንገዶችን ለመገንባት ሞክረን ነበር፤ ነገር ግን መኪና አሽከርካሪዎች ሃሳቡን በመቃወማቸው ተውነው'' ይላሉ የጣልያኗ ሚላን ከተማ ምክትል ከንቲባ ፒዬርፍራንሴስኮ ማራን።
በሰሜናዊ ጣልያን የምትገኘው የፋሽን ኢንዱስትሪ ማዕከሏ ሚላን ሰዎች በቀላሉ እንዲንቀሳቀሱ ለማገዝ ብስክሌት ላይ ኢንቨስት ማድረግ ከጀመሩ የአውሮፓ ከተሞች መካከል የመጀመሪያዎቹ ውስጥ ትጠቀሳለች።
አዲስ 35 ኪሎ ሜትር የብስክሌት መንገድ ብትገነባም አብዛኛዎቹ መንገዶች ግን ጊዜያዊ ናቸው።
''በአሁኑ ሰአት ብስክሌት የሚጠቀሙ ሰዎች ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ የሕዝብ ትራንስፖርት ነበር የሚጠቀሙት። ነገር ግን አሁን ላይ ሌላ አማራጭ አስፈልጓቸዋል። ከኮቪድ-19 በፊት በከተማችን ዋና የግብይት ጎዳናዎች ላይ 1 ሺግ ገደማ ሳይክል የሚጋልቡ ሰዎች የነበሩ ሲሆን አሁን ግን ቁጥሩ ወደ 7 ሺህ ከፍ ብሏል"።
በዚህ የጣልያን ክፍል ውስጥ መንግሥት የብስክሌት ዘርፉን ለማበረታታት በማሰብ 115 ሚሊየን ዩሮ ፈሰስ ያደረገ ሲሆን ሳይክል መግዛት ለሚፈልጉ ዜጎች ደግሞ እስከ 500 ዩሮ ድረስ የዋጋ ቅናሽ እንደሚያደርግ አስታውቋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በፈረንሳ መዲና ፓሪስ ደግሞ ከኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት በኋላ ከብስክሌት ጋር ለተያያዙ መሰረተ ልማቶች እስከ 20 ሚሊየን ዩሮ ድረስ ወጪ ተደርጓል።
በፈረንሳይ ከዚህ በተጨማሪ የብስክሌት ተጠቃሚዎች ቁጥር በ27 መቶ ከፍ ብሏል። ለዚህ ደግሞ ዋነኛ ምክንያቱ የፈረንሳይ መንግሥት ዜጎች ብስክሌታቸውን ለማሳደስ ሲፈልጉ የ50 ዩሮ ድጎማ ማድረግ በመጀመሩ ነው ተብሏል።
በአምስተርዳም ደግሞ ከወረርሽኙ በፊት ለብስክሌት የሚሆን መሰረተ ልማት በአግባቡ ተዘርግቶ ነበር። የኔዘርላንዷ ዋና ከተማ በብስክሌተኞች የምትታወቅ ሲሆን 767 ኪሎ ሜትር እርዝማኔ ያለው የብስክሌት መንገድም አላት።
በኔዘርላንድ በአሁኑ ወቅት በጣም እየተቸበቸበ የሚገኘው የብስክሌት አይነት በኤሌክትሪክ የሚሰራው ነው። በተጨማሪም በብስክሌት እቃዎችና ምግቦችን ወደ ሰዎች ቤት የማድረስ ስራ 53 በመቶ ጨምሯል በኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝ ዘመን።
በአሁኑ ሰአት በርካታ ከተሞች ወደፊት ምን ሊፈጠር እንመዲችል ባለማወቃቸው ከዚህ በኋላ ስለሚኖሩ የእንቅስቃሴ አይነቶች ቆም ብለው እያሰቡ ነው። ወረርሽኙም ሕይወት ምን ሊመስል እንደሚችል በትንሹም ቢሆን አሳይቷል።
አሁን ባለው አካሄድ ደግሞ ብስክሌትን እንደ አማራጭ የትራንስፖርት ዘዴ መጠቀም ስኬታማነቱ ታይቷል። ነገር ግን በበርካታ የአውሮፓ ከተሞች ዋናው ጥያቄ ብስክሌትን በቋሚነት መጠቀም አለብን ወይስ የለብንም የሚለው ሆኗል።












