አርሜንያ እና አዘርባጃን በአወዛጋቢው ክልል ተጋጩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ናጎርኖ- ካራባክ ተብሎ በሚታወቀው አወዛጋቢ ክልል ውስጥ የአርሜንያናና የአዘርባጃን ወታደሮች መጋጨታቸው ተዘገበ።
የአርሜንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኒኮል ፓሺንያን እንዳስታወቁት የአዘርባጃን ወታደሮች በአየር እና በዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች በመታገዝ ጥቃት ሰንዝረዋል።
አክለውም የአርሜንያ ወታደሮች በበኩላቸው በሰጡት ምላሽ ሁለት የአዘርባጃን ሄሊኮፕተሮችን እና ሶስት ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ተኩሰው መጣላቸውን አስታውቀዋል።
አዘርባጃን በበኩሏ አርሜንያ በአወዛጋቢው ክልል መስመር ላይ ተቀጣጣይ ፈንጂዎችን በመጠቀም ዘመቻ መክፈቷን ገልጻለች።
ናጎርኖ- ካራባክ የተባለውን ክልል ተከትሎ ለረዥም ዓመታት የቆየው ይህ የሁለቱ አገራት ፍጥጫ ባለፉት ወራት እንደገና ማገርሸት ጀምሯል።
ባሳለፍነው ሐምሌ ወር ላይም በድንበር አካባቢ በተቀሰቀሰ ግጭት ምክንያት 16 ሰዎች መሞታቸው የሚታወስ ነው።
አርሜንያ እና አዘርባጃን በጎሮጎሳውያኑ 1991 የቀድሞዋ ሶቭየት ሕብረት ከመፍረሷ በፊት ሁለቱም የሕብረቱ አካል ነበሩ።
ላለፉት አራት አስርት ዓመታትም ሁለቱም ይገባኛል በሚሉት ናጎርኖ- ካራባክ አካባቢ ሲጨቃጨቁ ቆይተዋል። አካባቢው በአሁኑ ሰአት በአርሜንያ ብሄሮች ቁጥጥር ስር ይሁን እንጂ የዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ግን ቦታው የአርባጃን እንደሆን ተስማምቷል።
በጎሮጎሳውያኑ 2016 ተመሳሳይ ግጭት ተከስቶ ለአራት ቀናት የቆየ ጦርነት መሰል ውጊያ አካሂደዋል።












