ሩሲያ ፡ በገዳይ መርዝ ተመርዞ የነበረው አሌክሴ ናቫልኒ ከሆስፒታል ወጣ

አሌክሴ ናቫልኒ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, አሌክሴ ናቫልኒ

በገዳይ መርዝ ተመርዞ የነበረው እውቁ የሩሲያው ፕሬዝደንት ተቀናቃኝ አሌክሴ ናቫልኒ ከህመሙ አገግሞ ከበርሊን ሆስፒታል ወጣ።

እውቁ የጀርመኑ ሻርሌት ሆስፒታል የአሌክሴ የጤና ሁኔታ በመሻሻሉ ከሆስፒታል ውጪ ሆኖ ህክምናውን መከታተል ይችላል ሲል አስታውቋል። አሌክሴ ለ24 ቀናት በጽኑ ሕሙማን ክፍል መቆየቱን እና አሁን ያለበትን ሁኔታ ከግምት በማስገባት ሙሉ ለሙሉ ሊያገግም እንደሚችል ሆስፒታሉ ገልጿል።

አሌክሴ ያለ ምንም ድጋፍ ቆሞ የሚያሳየውን ምስሉን በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ካወጣ በኋላ ሃኪሞች እንዲያገግም የተቻላቸውን ሁሉ እንዳደረጉት ጽፏል። አሌክሴ ጀርመን ከገባ በኋላ በተደረገለት ምርመራ የነርቭ ስርዓትን በሚያውክ ኖቪቾክ በተሰኘ መርዝ መመረዙን ውጤቶች አረጋግጠዋል።

ፑቲን የሥልጣን ዘመናቸውን ማራዘማቸው ትክከል አይደለም፣ ሕገ መንግሥቱን ጥሰዋል፣ ሥልጣን ማራዘማቸው መፈንቅለ መንግሥት ከማድረግ አይተናነስም ሲል አሌክሴ በተደጋጋሚ በፕሬዝደንቱ ላይ የተቃውሞ ድምጽ በማሰማት ይታወቃል።

ከአንድ ወር ገዳማ በፊት ከሩሲያዋ ቶምስክ ከተማ ወደ ሞስኮ እየበረረ ሳለ ከፍተኛ ሕመም ስለተሰማው አውሮፕላኑ በድንገት ኦምስክ፣ ሳይቤሪያ እንዲያርፍ ተገዶ ነበር።

አሌክሴ አውሮፕላኑን ከመሳፈሩ በፊት በቶምስክ አውሮፕላን ጣቢያ ቁጭ ብሎ ሻይ ሲጠጣ የሚያሳይ ፎቶ ተለቆ ነበር። የአሌክሴ ደጋፊዎች እና ቡድን አባላት አሌክሴ ከሻይ ጋር ተቀላቅሎ በተሰጠው መርዝ መመረዙን ይናገራሉ። ለዚህም ፑቲንን ተጠያቂ ያደርጋሉ። ክሬምሊን ግን ስለ ጉዳዩ የማውቀው ነገር የለም ይላል።

አሌክሴ ወደ ጀርመን ለህክምና ከተወሰደ በኋላ የተደረጉለት መርመራዎች የነርቭ ስርዓትን በሚያውክ መርዝ መመረዙን አረጋግጠዋል። ለአሌክሴ ቀድመው ሕክምና ያደረጉት የሩሲያ ሃኪሞች አሌክሴ ስለመመረዙ ምንም አይነት ማረጋገጫ የለም ብለው ነበር።