ፖለቲካ ፡ ለውጥ ለማምጣት የምን ያህል ሰዎች ተሳትፎን ይፈልጋል?

ከአድማ በታኝ ፖሊሶች የቆመች ሴት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

አንድን መሪ ከሥልጣን ለማስወገድ ምን ያህል ሰው መቃወም አለበት? የሚያዋጣው ነውጥ የቀላቀለ ተቃውሞ ነው ወይስ ሰላማዊ?

ከማይዘነጉ ንቅናቄዎች መካከል እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1980ዎቹ የነበረው የፖላንድ ተቃውሞ፣ የደቡብ አፍሪካው የጸረ አፓርታይድ ትግል፣ የቱኒዝያውን ፕሬዘዳንት ያስወገደው የጃዝሚን አብዮት እና የፀደይ አብዮት (አረብ ስፕሪንግ) ይጠቀሳሉ።

እነዚህ ጉልህ ለውጥ ማምጣት የቻሉ ንቅናቄዎች ናቸው።

ወደ ቅርብ ጊዜ አብዮት ስንመጣ ደግሞ ቤላሩስን እናገኛለን። ፕሬዘዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ ምርጫ አሸንፌያለሁ ማለታቸውን ተከትሎ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለተቃውሞ ወጥተዋል።

በርካቶች ታስረዋል፣ ስቃይና እንግልት እንደደረሰባቸው የሚናገሩም አሉ። ሆኖም ግን ተቃውሞው ሰላማዊ በሆነ መንገድ ቀጥሏል።

ለመሆኑ ተቃውሞው ግቡን ይመታል? የሚለውን ለመመለስ ታሪክን መመልከት ያሻል።

ነውጠኛ ተቃውሞ የቱ ነው?

የሀርቫንድ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንቲስት ኤሪካ ቼንዌዝ በአምባገነን ሥርዓቶች ላይ ስለሚነሳ ተቃውሞ አጥንተዋል። አምባገነናዊ ሥርዓት ውስጥ ሕዝብ መሪውን ለማስወገድ ምርጫ ማካሄድ አይችልም።

ስለ ተቃውሞ ሲነሳ የትኛው ነውጥ የቀላቀለ የትኛውስ ሰላማዊ ነው? የሚለውም ያከራክራል።

ንብረት ሲወድም ተቃውሞው ነውጠኛ ነው ይባላል? ሰዎች አካላዊ ጥቃት ሳያደርሱ ዘረኛ ስድብ ቢሳደቡስ? ራስን ማቃጠል ወይም የረሀብ አድማ መምታትስ ነውጥ የቀላቀሉ የተቃውሞ መንገዶች ናቸው?

ለእያንዳንዱ ሁኔታ ግልጽ በሆነ መንገድ ነውጠኛ ወይም ኢ-ነውጠኛ የሚል ትርጓሜ መስጠት ይከብዳል። ሆኖም ግን ነውጥ በቀላቀለና በሰላማዊ ተቃውሞ መካከል ያሉ ልዩነቶችን መረዳት እንችላለን።

ለምሳሌ ሰውን መግደል ነውጠኛ መሆኑ አያጠያይቅም። ሰላማዊ ሰልፍ፣ ፊርማ ማሰባሰብ፣ አድማ መምታትና አንድን ሁነት ረግጦ መውጣት ሰላማዊ ተቃውሞ ናቸው።

አንድ ጥናት 198 አይነት ሰላማዊ ተቃውሞዎች እንዳሉ ያሳያል።

አድማ በታኝ ፖሊሶች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ሳይንቲስቷ ከ1990 እስከ 2006 በተሰበሰበ መረጃ ላይ ጥናት ሠርተው፤ ሰላማዊ ተቃውሞ ውጤታማ የመሆን እድሉ ሰፊ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል።

ሰላማዊ ተቃውሞ ውጤት ያስገኛል?

ነውጥ የቀላቀለ ተቃውሞ ድጋፍ ሊያጣ እንደሚችል ተመራማሪዎች ይናገራሉ። ሰላማዊ ተቃውሞ ሲካሄድ የሚቀላቀሉ እንደሚበራከቱ፣ በአጭር ጊዜና ያለ ምንም ልዩ ስልጠና ሊከናወን እንደሚችልም ያክላሉ።

ታዳጊዎች፣ አካል ጉዳተኞች፣ ሴቶች እና አዛውንቶች ሰላማዊ ተቃውሞ ይቀላቀላሉ።

ቡልዶዘር አብዮትን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ወታደሮች ለምን ተቃዋሚዎች ላይ እንዳልተኮሱ ሲጠየቁ፤ ተቃዋሚዎቹን ስለምናውቃቸው ነው ብለው ነበር።

ተቃዋሚዎቹ ጓደኞቻቸው፣ የአክስታቸው ልጆች፣ ጎረቤቶቻቸው ወዘተ. . . ነበሩ።

የፖለቲካ ሳይንቲስቷ ኤሪካ እንደሚሉት፤ 3.5 በመቶ ሕዝብ ከተቃወመ ለውጥ ማምጣት ይችላል።

ቤላሩስን ማሳያ ብናደርግ፤ 3.5 በመቶ ማለት ከአገሪቱ ዘጠኝ ሚሊዮን ዜጎች 300,000 ማለት ነው።

በመዲናዋ ሚንስክ በተካሄደው ተቃውሞ ወደ አስር ሺህ ሰዎች ተሳትፈዋል። አሶሽየትድ ፕሬስ 200,000 ተቃዋሚዎች መገኘታቸውን የዘገበበት ወቅት ነበር።

3.5 በመቶ የሚለው ቁጥር በሁሉም አገር ይሠራል ማለት አይደለም። አንዳንድ ንቅናቄዎች በአነስተኛ ቁጥርም ግባቸውን መተዋል። ከፍተኛ ሕዝብ አሳትፈው የከሸፉ አብዮቶችም አሉ። ለዚህ የ2011 የባህሬን እንቅስቃሴ ይጠቀሳል።

በመላው ዓለም ከትጥቅ ትግል ይልቅ ሰላማዊ ተቃውሞ እየተዘወተረ የመጣ የትግል ስልት መሆኑን የኤሪካ ጥናት ይጠቁማል።

ከ2010 እስከ 2019 ባሉት ዓመታት የታዩ ተቃውሞዎች በሰው ልጅ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ሰላማዊ ናቸው።

በሌላ በኩል ከአስር ነውጥ የቀላቀሉ ተቃውሞዎች ዘጠኙ ይከሽፋሉ። በቀደመው ዘመን ከሁለት ሰላማዊ ተቃውሞዎች አንዱ ይሳካ ነበር። አሁን ላይ ከሦስት ሰላማዊ ተቃውሞዎች ፍሬያማ የሚሆነው አንዱ ብቻ ነው።

መንግሥት ግልበጣ

ከ2006 ወዲህ አንዳንድ ለውጦች እየተስተዋሉ ነው። የሱዳኑ ኦማር አልበሽር ከሥልጣን ተወግደው በሳምንታት ውስጥ የአልጄሪያው ፕሬዘዳንት አብዱልአዚዝ ቡተፍሊካም ተመሳሳይ እጣ ደርሷቸዋል።

እንዲህ አይነት የመንግሥት ግልበጣዎች ቁጥር እየቀነሰ ነው።

የማኅበራዊ ሚዲያ ዘመን ላይ እንደመሆናችን ዲጂታል አብዮት ሲቀጣጠል እናያለን። መረጃ በቀላሉ ይንሸራሸራል። ቀጣዩ የተቃውሞ ሰልፍ የት እንደሚካሄድ ለማወቅም አይከብድም።

ሆኖም ግን ዲጂታል አብዮትን እንዴት ማስተጓጎል እንደሚቻል መሪዎች ያውቃሉ።

ኤሪካ እንደሚሉት፤ መሰል አብዮቶችን ለማስቆም የዲጂታል ስለላ እና ሰርጎ ገብ እርምጃዎች ይወሰዳሉ። በማኅበራዊ ሚዲያ ሐሰተኛ መረጃ እና ፕሮፓጋንዳም ይነዛል።

በቤላሩስ ተቃዋሚዎች ስልካቸው እየተፈተሸ ነው። እንደ ቴሌግራም ባለ መልዕክት መለዋወጫ ስለ ተቃውሞው መረጃ አግኝተው እንደሆነም ይጣራል።

የቴሌግራም ቡድን የከፈቱ ሰዎች ታስረዋል። ቴሌግራም በበኩሉ የቡድኑ አባላት ዝርዝር ፖሊስ እጅ ከመግባቱ በፊት ቡድኖቹ እንዲከስሙ ያደርጋል።

ታዲያ ፕሬዘዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ ሥልጣናቸውን ይዘው ይቆዩ ይሆን? ወይስ ተቃዋሚዎች ድል ይነሳሉ? አብረን የምናየው ይሆናል።