ቤላሩስ፡እንግልት፣ ግርፋትና ስቃይ ያስከተለው የቤላሩስ ምርጫ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች በቤላሩስ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ እያሉ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉ ዜጎች ላይ ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይል እየተወሰደ እንደሆነ እየገለጹ ነው።
በተጨማሪም ታሳሪዎቹ ግርፋትና ማሰቃየት እደረሰባቸው እንደሆነም ይናገራሉ።
እስካሁን 6 ሺህ 700 የሚሆኑ በፖሊስ በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩ ሰዎች የተለቀቁ ሲሆን በነበራቸው ቆይታ በርካታ የመብት ጥሰቶች እንደተፈጸሙባቸው እየገለጹ ይገኛሉ።
አምነስቲ ኢንተርናሽናልም በበኩሉ ሰዎችን ማሰቃየት በስፋት እየታየ ነው ብሏል። በቤላሩስ እየተካሄደ ያለው የተቃውሞ ሰልፍ አምስተኛ ቀናትን ያስቆጠረ ሲሆን የሰልፈኞች ዋነኛ ጥያቄ ደግሞ የምርጫ ውጤት ተጭበርብሯል የሚል ነው።
ባሳለፍነው እሁድ በተካሄደው ምርጫ ፕሬዝደንት ሉካሼንኮ አሸናፊ መሆናቸው በምርጫ ኃላፊዎች ተገልጿል። ነገር ግን የተቃዋሚ ተፎካካሪዋ ስቬትላና ቲካኖቭስካያ ደጋፊዎች አሸናፊዋ እሷ ናት በማለት ተቃውሟቸውን እየገለጹ ያሉት።
የካቢኔው ቃል አቀባይ ናታላያ ኮቻኖቫ በቴሌቪዥን ባስተላለፉት መልዕክት ፕሬዝዳንቱ በተቃዋሚ ሰልፈኞች ላይ ስለተወሰደው እርምጃ ይፋዊ ምርመራ እንዲደረግ ማዘዛቸውንና ከአንድ ሺ በላይ ሰዎች ደግሞ መፈታታቸውን ገልጸዋል።
ከእስር የተፈቱት ሰዎች በማህበራዊ ሚዲያዎች እያጋሯቸው በሚገኙ ምስሎች ላይ በርካቶች ድብደባና ማሰቃየት ደርሶባቸው እንደነበር እያሳዩ ነው። አንዳንዶቹ ያበጠና የቆሰለ የሰውነታቸውን ክፍል ፎቶ በማንሳት ይፋ አድርገዋል። ጉዳቱን ያደረሰብንም ፖሊስ ነው ገልጸዋል።
'' ሰዎችን በጭካኔ ይገርፋሉ፤ ያለምንም ክስ ሁሉንም ሰው በቁጥጥር ስር እያዋሉ ነው። በአንድ ክፍል ውስጥ ሌሊቱን በሙሉ ቆመን እንድናሳልፍ ተደርገናል። ሴቶች እየተገረፉ የድረሱልን ድምፅ ሲያሰሙም ሰምተናል። እንዲህ አይነት ጭካኔ ምንም አይገባኝም'' ሲል አንድ ግለሰብ ለቢቢሲ ተናግሯል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ከታሳሪዎች አገኘሁት ባለው መረጃ መሰረት ሰዎች ራቁታቸውን እንዲሆኑ ተደርገው ተገርዋል፤ እንዲሁም የመድፈር ማስፈራራት ደርሶባቸዋል።
'' በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩ ሰዎች እንደነገሩን ማቆያ ማዕከላቱ ወደ ማሰቃያ ማዕከልነት ተቀይረዋል። ለተቃውሞ የወጡት ዜጎች ቆሻሻ አፈር ላይ እንዲተኙ በማድረግ ፖሊስ ይደበድባቸውና ያስፈራራቸው ነበር'' ብላለች በድርጅቱ የምስራቅ አውሮፓ እና ማዕከላዊ እስያ ዳይሬክተር ማሪ ስትሩተርስ።
አንድ የቢቢሲ ጋዜጠኛ ባገኘው የድምጽ ማስረጃ ላይ ደግሞ በዋና ከተማዋ ሚንስክ በሚኘውና ኦክሬስቲና በሚባለው ማዕከል ውስጥ ሰዎች ሲጮሁ ይሰማል።
የአገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትሩ ዩሪ ካራዬቭ በተቃውሞ ሰልፈኞች ላይ ለተወሰደው እርምጃ ኃላፊነቱን እንደሚወስዱ በመግለጽ በግጭቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ደግሞ ይቅርታ ጠይቀዋል።
ታዛቢዎች እንደገለጹት መንግሥት በደረሰበት ዓለማቀፋዊ ጫና ምክንያት ቢሆንም በርካታ ሰዎችን እየለቀቀ ይገኛል። የአውሮፓ ሕብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችም ቢሆኑ ቤላሩስ ላይ ማዕቀብ ለመጣል እየተዘጋጁ ነበር ተብሏል።
ባለስልጣናት እንደገለጹት ተፈጥሮ በነበረው አለመረጋጋትና ግጭት ምክንያት ሁለት ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል። አንደኛው ግለሰብ በተቃውሞ ቦታው ላይ ሰኞ ዕለት የተገደለ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ ነው ሕይወቱ ያለፈችው።
በቤላሩስ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሰዎች ላይ ደረስ የተበለው የመብት ጥሰትና አካላዊ ጉዳት መጠን ከዚህም በላይ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል። በቁጥጥር ስር ከዋሉት ሰዎች መካከል ተቃዋሚዎች፣ ጋዜጠኞችና በመንገድ ላይ ሲያልፉ የነበሩ ሰዎች ይገኙበታል።
በቁጥጥር ስር ውሎ የነበረው ጋዜጠኛ ኒኪታ ቴሊዜንኮ በአንድ ቀን ውሎው ያጋጠመውን እና ያስተዋለውን ሁኔታ ዘርዝሮ ጽፏል። ሁኔታውን ሲገልጽም ''ሰዎች አንድ በአንዱ ላይ ተደራርቦ መሬት ላይ ይተኙ ነበር፤ አንዳንዶቹም በደምና በሰገራ ተበክለው ይታያሉ። መጸዳጃ ቤት እንዲጠቀሙ አይፈቀድላቸውም ነበር። ሌላው ቀርቶ ጀርባን ለማሳረፍ መገላበጥ እንኳን ክልክል ነበር'' ብሏል።
አክሎም በርካታ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችን እንደተመለከተ ገልጿል። ''እግራቸው የተሰበረና አካላቸው ላይ ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው በርካቶች ነበሩ። ህክምና እንዳያገኙ መደረጋቸው አልበቃ ብሎ ጠባቂዎቹ እንደገና ይደበድቧቸው ነበር''
በማህበራዊ ሚዲያ በተለቀቀ አንድ ተንቀሳቃሽ ምስል ላይ ደግሞ የተቃዋሚ መሪዋ ማሪያ ዋና ከተማዋ ሚንስክ ውስጥ አበባ በመያዝ ሴት ሰልፈኞችን ሲቀላቀሉ ታይተዋል።
የተቃዋሚ መሪዋ ባለቤታቸው በቁጥጥር ስር ውሎ የመምረጥ መብቱን እስከሚነጠቅ ድረስ በቤት ልጆቻቸውን በመንከባከብ የሚያሳልፉ የቤት እመቤት ነበሩ። በአሁኑ ሰአት ግን የፕሬዝዳንቱ ዋነኛ ተፎካካሪ በመሆን በርካቶችን ከጎናቸው ማሰለፍ ችለዋል።












