ቤላሩስ ፡ ስለ ቤላሩስ ብዙ ሰው የማያውቃቸው አራት አስገራሚ ነገሮች

ቤላሩስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቤላሩስን ብዙ ሰው አያውቃትም፡፡ እንደኛው ወደብ አልባ አገር ናት፡፡ በምሥራቅ አውሮፓ ነው የምትገኘው፡፡ ሩስያ፣ ዩክሬን፣ ፖላንድና ላቲቪያ ያዋስኗታል፡፡

ካለፈው እሑድ ጀምሮ የዓለም ሚዲያ ትኩረት ስባለች፡፡ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ ለ6ኛ ጊዜ ምርጫ አሸነፍኩ ብለዋል፡፡

ለመሆኑ ስለ ቤላሩስ ምን ለየት ያለ ነገር አለ?

አራት አስገራሚ ነገሮችን እንንገራችሁ፡፡

1ኛ፡- በ2ኛው የዓለም ጦርነት 25 ከመቶ ሕዝቧን አጥታለች

ብዙ ሰዎች ቤላሩስ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ውስጥ ነበረችበት እንዴ ሊሉ ይችላሉ፡፡ አዎ ነበረችበት፡፡ እንዲያውም በጦርነቱ ዋነኛ ተጎጂ አገር እንደ ቤላሩስ የለም፡፡

ምን ያህል ሕዝብ የሞተባት ይመስላችኋል? 1.6 ሚሊዮን ንፁሕ ዜጎችና 600,000 ወታደሮቿ አልቀዋል፡፡ ቤላሩስ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ የአይሁድ ዝርያ ያላቸው ቤላሩሳዊያን ሁሉም ማለት ይቻላል አልቀዋል፤ በ2ኛው የዓለም ጦርነት፡፡

ዋና ከተማዋ ሚንስክ ትባላለች፡፡ ይቺ ከተማ 85 ከመቶ ወድማ ነበር በሁለተኛው የዓለም ጦርነት፡፡ አንድ ሰው ከጦርነቱ በፊት ይቺን ከተማ ለቆ ከነበረና ከጦርነቱ በኋላ ቢመለስ ከተማዋን በመልክ ሊያውቃት ፈጽሞ በማይቻልበት ደረጃ ነበር የወደመችው፡፡

መልሳ የተገነባችው በ1950ዎቹና 60ዎቹ ነው፡፡

2ኛ፡- የአውሮ የመጨረሻው አምባገነን

ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ በአውሮፓ ባልተለመደ ሁኔታ ሥልጣናቸውን ርስት አድርገውት ቁጭ ብለዋል፡፡ ይኸው ስንት ዘመን ከቤተ መንግሥት አልወጣ ካሉ፡፡ 26 ዓመታት!

በአውሮጳ እንዲህ ሥልጣኑን የሙጥኝ ያለ ሰው እንዳለ ብዙ ሰው አያውቅም፡፡

ሉካሼንኮ የይስሙላ ምርጫ ያደርጋሉ ተብለው ይታማሉ፡፡ ሁልጊዜም በከፍተኛ ድምጽ ያሸንፋሉ፡፡ ለምሳሌ በእሑዱ ምርጫ 80 ከመቶ ሕዝቤ መርጦኛል ብለው ይኸው ተቃውሞ ተነስቶባቸዋል፡፡

የአሁኑ ተቃውሞ ትንሽ ጠንከር፣ ጠጠር ያለ ይመስላል፡፡

ሰውየው ወደ ሥልጣን የመጡት ድሮ ነው፡፡ እንደነርሱ አቆጣጠር በ1994 ዓ.ም፡፡ ለዚያም ነው ‹‹የመጨረሻው የአውሮፓ አምባገነን›› በሚል ቅጽል ስም የሚጠሩት፡፡

ሉካሼንኮ አንድ ወቅት ላይ ምናሉ መሰላችሁ፡፡ «ከኔ ፓርቲ ሌላ ተቃዋሚ ፓርቲ የሚገባ ሰው አሸባሪ ነው፡፡ ስለዚህ አንገቱን እንደ ዶሮ ይዤ እቀነጥሰዋለሁ፡፡»

3ኛ፡- ፕሬዝዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲን የገደለው ሰው

ሊ ሃርቬይ ኦስዉልድ ቀድሞ የአሜሪካ የባሕር ኃይል አባል ነበር፡፡ ወደ ቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረት ሲደርስ ገና 20 ዓመቱ ነበር፡፡ ማርክሲስት ሆኛለሁ ይል ነበር ያኔ፡፡

ከዚያ የሶቭየት ኅብረት የስለላ ድርጅት ኬጂቢ ለመግባት አመለከተ፡፡

ማመልከቻው ውድቅ ተደረገበት፡፡ ያን ቀን የቱሪስት ቪዛው ይቃጠልበት ነበር፡፡ ኦስዋልድ ተናደደና አንዱን እጁን ሰበረው፡፡ የገዛ እጁን፡፡ ነገሩ ልዩ ትኩረት እንዳይስብ ስለተፈራ ሶቭየቶች እንዲቆይ ፈቀዱለት፡፡

ከዚያ ወደ ሚንስክ ከተማ ተላከና የሬዲዮና ቴሌቪዥን ማምረቻ ፋብሪካ ውስጥ ሥራ ጀመረ፡፡ በቤላሩስ ዋና ከተማ ሚኒስክ አንድ ከፍል ቤት ተሰጥቶት መኖር ጀመረ፡፡

ኦስዋልድ ያን ጊዜ በዚያች ከተማ ብቸኛው አሜሪካዊ ነበር፡፡

በመጋቢት 1961 ማሪና ፕሩሳኮቫን አገባ፡፡ በዓመቱ ሴት ልጅ ወለዱ፡፡ ከዚያ በዓመቱ ደግሞ ወደ አሜሪካ አቀኑ፡፡

ከዚያ በዓመቱ ኅዳር ወር ላይ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የነበሩትን ጆን ኤፍ ኬኔዲን በዳላስ ቴክሳስ ተኩሶ ገደላቸው፡፡እና ይህ ነፍሰ ገዳይ ሲታሰብ እሱ የኖረባት ቤላሩስ አብራ ትነሳለች፡፡

4ኛ፡- በዓለም እጅግ አደገኛው የኒክሌር ጨረር ብናኝ 70 ከመቶ የሚገኘው በቤላሩስ ነው

በሚያዝያ 1986 በዩክሬን፣ ቼርኖቢል ከሚገኙት ከአራቱ የኒክሌር ማብሊያዎች ውስጥ አንዱ ፈነዳ፡፡ እስከዛሬ በዓለም ላይ በኒክሌየር ምርት መጥፎ አጋጣሚ ተደርጎ የሚታሰበው ይህ ክስተት ነው፡፡

እጅግ አደገኛና መርዛማ የሆነው ይህ የጨረር ኬሚካል ብናኝ ታዲያ ከዩክሬን ይልቅ የጎዳው ቤላሩስን ነው፡፡ የራዲዮአክቲቭ ጨረር ያረፈው በቤላሩስ መሬት ላይ ነበር፡፡

በዚህም አንድ አምስተኛው የአገሪቱ የእርሻ መሬት በመርዛማው ብናኝና ዝቃጭ በክሎታል፡፡ በዚህ የተነሳ 2ሺ ከተሞችና መንደሮች ፈርሰዋል፡፡ ግማሽ ሚሊዮን ሰዎች ሌላ ቦታ እንዲሰፍሩ ሆነዋል፡፡

ሁለት ሚሊዮን ቤላሩሳዊያን አሁንም በአደገኛ ቀጠና ውስጥ ነው የሚኖሩት፡፡ ቤላሩስ በዚህ የኒክሌር ብናኝና ዝቃጭ ጣጣ 300 ቢሊዮን ዶላር አጥታለች፡፡ መከራዋ እስከዘላለሙ ሊቀጥል ይችላል፡፡