ኢትዮጵያና ኤርትራን ጨምሮ ሌሎች ሃገራት ገናን ለምን ታኅሣሥ 29 ያከብራሉ?

ኢትዮጵያ እና ገናን ዛሬ እያከበሩ ያሉ 16 ሃገራት

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency

አውሮጳና አሜሪካ ገና ያከበሩት ታኅሣሥ 15 ዕለተ ረቡዕ ነበር። ኢትዮጵያና ኤርትራ እንዲሁም የተወሰኑ ሌሎች ሃገራት ግን ገናን ዛሬ [ታኅሣሥ 28] እያከበሩ ይገኛሉ።

እነዚህን ሃገራት የሚያመሳስላቸው አንድ ጉዳይ የኦርቶዶክስ ኃይማኖት ነው። ሌላኛው ደግሞ የቀን አቆጣጠር።

ከአፍሪካ፤ ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና ግብፅ [በተለይ የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤ/ክ እምነት ተከታዮች] ያሉ ክርስትያኖች ገናን በየዓመቱ ታኅሣሥ 29 [በአራት ዓመት አንድ ጊዜ ደግሞ ታኅሣሥ 28] ያከብራሉ።

አብዛኛዎቹ ምዕራባውያን ሃገራት የግሪጎሪን የቀን አቆጣጠር ነው የሚከተሉት። የቀን አቆጣጠሩን የተፈጠረው በ1582 በሊቀ-ጳጳስ ግሪጎሪ ነበር።

አብዛኛዎቹ የቀድሞዋ ሶቪየት ሕብረትና የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ደግሞ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ45 በጁሊየስ ቄሳር የተፈጠረውን የጁሊያን ቀን አቆጣጠር የሚከተሉ ናቸው።

አሁንም ቢሆን በርካታ አገራት ኦፌሴላዊ የቀን አቆጣጠራቸውን በግሪጎሪ አድርገው ለአገር አቀፍ በዓላት ጁሊያንን የሚጠቀሙ አሉ።

ከላይ የተጠቀሱትን ኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ግብፅን ጨምሮ፡

  • ሩስያ
  • ሰርቢያ
  • ቤላሩስ
  • ሞንቴኔግሮ
  • ካዛኪስታን
  • እስራኤል
  • ቡልጋሪያ
  • መቄዶኒያ
  • ጆርጂያ
  • ሞልዶቫ - ዛሬ የእየሱስ ክርስቶስን ልደት እያከበሩ የሚገኙ ሃገራት ናቸው።

ግሪክ፣ ቆጵሮስና ሮማኒያ የሚገኙ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ግን ገናን ያከበሩት በግሪጎሪ አቆጣጠር፤ ማለትም ታኅሣሥ 15 ነው።

ከላይ ካሉት 14 ሃገራት በተጨማሪ አርሜኒያ በራሷ የቀን አቆጣጠር ነው ገናን የምታከብረው። አርሜኒያ ገናን ታኅሣሥ 28 [በአራት ዓመት አንዴ 27] ታከብራለች።

ኢትዮጵያ

ኢትዮጵያ የራሷ ቀን አቆጣጠር ያላት አገር ናት። የቀን አቆጣጠሩ ከኮፕቲክ ኦርቶዶክስ እምነት ቀን አቆጣጠር ጋር ተመሳሳይነት አለው።

ልክ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ገናን ከምዕራቡ ዓለም በ13 ቀናት ዘግይተው ያከብራሉ። ጥምቀትና የፋሲካ በዓልን የሚያከብሩበት ቀንም ከምዕራቡ በቀናት ልዩነት ያለው ነው።

ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የኦርቶዶክስ፣ ካቶሊክ፣ ኢቫንጀሊካል፣ እንዲሁም ጴንጤኮስታል እምነት ተከታዮች እና ሌሎች የክርስትና እምነት ተከታዮች ገናን የሚያከብሩት ዛሬ ነው።

ኤርትራ በበኩሏ ኦፌሴላዊ የቀን አቆጣጠሯን በግሪጎሪ ብታደርግም የክርስትና እምነት ተከታዮች ግን የኦርቶዶክስ ቀን አቆጣጠርን ይከተላሉ።

የሩስያው ፕሬዝደንት

የፎቶው ባለመብት, Mikhail Svetlov

የምስሉ መግለጫ, የሩስያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን የዘንድሮውን ገና ሴይንት ፒተርስበርግ የሚገኝ የኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ውስጥ ተገኝተው አክብረዋል

በዓለማችን ያሉ የኦርቶዶክስ እምነትም ሆነ የሌሎች ክርስትና ኃይማኖቶች ተከታዮች ገና ከመድረሱ በፊት ያሉትን ቀናት በፆም እንዲሁም በፀሎት ያስቧቸዋል።

የገና አከባበር ከአገር አገር የተለያየ ቅርፅ አለው። ለምሳሌ ሩስያ ውስጥ ያሉ ክርስትያኖች ከአዲስ ዓመት መባቻ እስከ ገና ያሉትን 7 ቀናት፣ በቀን 12 የተለያዩ ዓይነት ምግቦችን በመብላት ያሳልፋሉ። ዓላማው ደግሞ 12ቱን ሐዋሪያት ማሰብ ነው። ዩክሬን ውስጥ ደግሞ የበዓሉ አክባሪዎች ከቤት ቤት በመዘዋወር ዝማሬ በማሰማት ነው ቀኑን የሚያሳልፉት።

ቤላሩሲያውያን ለዕለቱ ቂጣና ዓሣ ያዘጋጃሉ። ሞንቴንግሮ ደግሞ ውስጡ ሳንቲም ያለበት ድፎ ዳቦ ይደፋሉ፤ ዳቦው ሲቆረስ መልካም ዕድል ይዞ እንደሚመጣ በማመን።

ሰርቢያ ውስጥ ገና የሚዘከረው ልክ እንደ ቡሄ ከጫካ ዛፍ ተቆርጦ ከተሰበሰበ በኋላ እሱን በማቃጠል በዙሪያው ተሰብስቦ እራት በመብላት ነው። ጆርጂያውያን ደግሞ ወደ አውራ ጎዳናዎች በመውጣት የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት ይዘክራሉ።

ኢትዮጵያም ቢሆን የበዓሉ መሠረት አንድ ቢሆንም አከባበሩ ከቦታ ቦታ ይለያያል። ነገር ግን አብዛኛው ምዕመን በዓሉን ወደ ቤተ እምነቶች በመሄድ፤ ከዚያ መልስም በጋራ ማዕድ በመቁረስ ያከብረዋል።