ቭላድሚር ፑቲን፡ "አስፈላጊ ከሆነ ወደ ቤላሩስ ፖሊስ እልካለሁ"

የፎቶው ባለመብት, ROSSIYA 1TV
የሩሲያው ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን አስፈላጊ ከሆነ ወደ ቤላሩስ ለመላክ ተጠባባቂ የፖሊስ ኃይል ማዘጋጀታቸውን አስታወቁ።
ፑቲን "የቤላሩስ ፕሬዚደንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ የተወሰነ ተጠባባቂ የፖሊስ ኃይል እንዳዘጋጅላቸው ጠይቀውኛል። እኔም ባሉኝ መሰረት አድርጌያለሁ" ሲሉ ነበር ለሩሲያ የመንግሥት ቴሌቪዥን የተናገሩት።
ነገር ግን በቤላሩስ ያለው ሁኔታ ከቁጥጥር ውጭ ካልሆነ በስተቀር ግን የፖሊስ ኃይሉን ላለመጠቀም መስማማታቸውን ፑቲን ለሮሲያ 1ቲቪ ገልፀዋል።
በምሥራቅ አውሮፓ የምትገኘው ቤላሩስ ሩስያ፣ ዩክሬን፣ ፖላንድና ላቲቪያ ያዋስኗታል።
ታዲያ በነሃሴ ወር መጀመሪያ ለ26 ዓመታት ያህል አገሪቷን እያስተዳደሩ ያሉት ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ ለ6ኛ ጊዜ ምርጫ አሸነፍኩ ማለታቸውን ተከትሎ ከፍተኛ ተቃውሞ ተቀስቅሶባት ነበር።
በወቅቱም የቢቢሲን ጨምሮ ቢያንስ 13 ጋዜጠኞች በዋና መዲናዋ ሚንስክ የተቃውሞ ሰልፎ ከመካሄዱ ቀደም ብሎ ታስረው ነበር።
የአገሪቷ የውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጋዜጠኞቹ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተወስደው የነበረው ማንነታቸውን ለማረጋገጥና ለመፈተሽ ነው ብለዋል። ይሁን እንጂ የቢቢሲው ስቲቭ ሮሰንበርግ "ድርጊቱ ዘገባቸውን ለማስተጓጎል የተደረገ ግልፅ ሙከራ ነበር" ብሏል።
ፕሬዚደንት ፑቲን ሩሲያ ከቤላሩስ ጋር ባላት የባህል፣ የቋንቋና የብሔር ትስስርን ጨምሮ የጠበቀ ወዳጅነት ስላላት በፀጥታው ዘርፍ የመደገፍ ግዴታ አለባት ብለዋል።
ይሁን እንጂ አዲስ ያዘጋጁት ተጠባባቂ የፖሊስ ኃይል፤ ገደብ ለመጣስ፣ በታጠቁ ኃይሎች ዝርፊያ ለማካሄድ፣ መኪኖችን፣ ቤቶችን፣ ባንኮችን ለማቃጠል፣ የመንግሥት ሕንፃዎችን ለመያዝ እና የመሳሰሉ ነገሮችን ለመፈፀም የፖለቲካ መፈክሮችን እንደ ሽፋን በመጠቀም ዋልታ ረገጥ የሆነ ተግባር ከሌለ በስተቀር ተጠባባቂ ኃይሉ ወደ ቤላሩስ እንደማይላክ አስታውቀዋል።
በአጠቃላይ በቤላሩስ ያለው ሁኔታ አሁን እየተረጋጋ መሆኑንም ፑቲን አክለዋል።
የፖላንዱ ጠቅላይ ሚኒስተር ማቴውስዝ ሞራዌኪ በበኩላቸው ፑቲን በቤላሩስ የተከሰተውን ዓለማቀፋዊ ሕግ ጥሰት ለመሸፋፈን በቤላሩስ ያለውን ፀጥታ እንደገና ለመመለስ የሚለውን ሃሳብ እንደ መሳሪያ እየተጠቀሙበት ነው ሲሉ ይከሳሉ።
በመሆኑም "ፑቲን የፖሊስ ኃይል ወደ አገሪቷ ልልክ እችላለሁ የሚለውን እቅዳቸውን አሁኑኑ ሊሰርዙ ይገባል" ብለዋል።
ሩሲያና ቤላሩስ የቀድሞ የሶቪየት ሕብረት አገራት [ሩሲያ፣ አርሜኒያ፣ ካዛኪስታን፣ ክይርጊስታን፣ ታጂኪስታን እና ኡዝቤኪስታን] በፈረንጆቹ 1992 የመሰረቱት የጦር ትብብር ድርጅት አባል ናቸው።
ሁለቱ አገራት ያላቸውን ትስስር የሚያጠናክር፣ ዜጎች የመስራት መብታቸው እንዲረጋገጥ እና ዜጎች በሁለቱም አገራት በነፃነት እንዲኖሩ የሚያስችል ሕብረት የመሰረቱትም በፈረንጆቹ 1996 ነበር።













