እስራኤልና ባህሬን ግንኙነታቸውን ለማሻሻል ስምምነት ላይ ደረሱ

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስቴር ቤንያሚን ናታንያሁና የባህሬን ልዑል ሳልማን ቢን ሃሚድ አል-ካሊፋ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

እስራኤልና ባህሬን ግንኙነታቸውን ሙሉ በሙሉ ለማሻሻል ስምምነት ላይ መድረሳቸውን የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተናገሩ።

"ሁለተኛዋ የአረብ አገር በ30 ቀናት ውስጥ ከእስራኤል አገር የሰላም ስምምነት ላይ ትደርሳለች።" ሲሉ ትዊተር ሰሌዳቸው ላይ አስፍረዋል።

ለበርካታ አስርታት በርካታ የአረብ አገራት እስራኤልን የፍልስጥኤም ጉዳይ ከተፈታ በኋላ ግንኙነታቸውን እንደሚቀጥሉ በመግለጽ አግልለው ነበር።

ነገር ግን ባለፈው ወር የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ ከእስራኤል ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሻሻል ስምንት ላይ ደርሳለች።

ከዚያ ጊዜ ወዲህ ባህሬን ትከተላለች የሚል ግምት ነበር።

በእስራኤል እና በአረብ ኤምሬትስ መካከል ያለው ግንኙነት የተለሳለሰው በአሜሪካ አሸማግይነት ሲሆን፤ ነሐሴ 13 ነበር ወዳጅነታቸውን ይፋ ያደረጉት።

በአብዛኛው የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ይህ ዜና በመልካም ቢወሰድም፤ ፍልስጥኤም ግን ተቃውሞዋን ገልጻለች።

በተለይም የአረብ ኤምሬትስ ለፍልስጥኤም እውቅና ካልሰጠችው እስራኤል ጋር ግንኙነት መፍጠራቸው፤ ፍልስጥኤምን መክዳት ነው ተብሏል።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ፤ ከአረብ ኤምሬትስ ጋር ዳግመኛ መወዳጀታቸውን አስታከው በወረራ የተያዘውን ዌስት ባንክ በግዳጅ የእስራኤል ይዞታ የማድረግ እቅዳቸውን ለማዘግየት ተስማምተዋል።