እስራኤል እና አረብ ኤሜሬቶች ታሪካዊ ከተባለለት ስምምነት ደረሱ

የፎቶው ባለመብት, Reuters/Getty Images
እስራኤል እና የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ግንኙነታቸውን ለማሻሻል ታሪካዊ ከተባለለት የሰላም ስምምነት መድረሳቸውን ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ይፋ አደረጉ።
ፕሬዝደንት ትራምፕ፣ የእስራኤሉ ቤንያሚን ኔታኒያሁ እና የአቡ ዳቢው ልዑል አልጋ ወረሽ ሞሐመድ አል ናሃያን በጋራ በሰጡት መግለጫ በሁለቱ አገራት መካከል የተደረሰውን ስምምነት "በመካከለኛው ምስራቅ ሰላም ለማስፈን ታሪካዊ እና ፈር ቀዳጅ ነው" ብለውታል።
በሁለቱ አገራት መካከል የተደረሰው ስምምነት እስራኤል አወዛጋቢውን በዌስት ባንክ የምታደርገውን የሰፈራ እቅዷን ያሰቆማል ተብሏል።
እስከዛሬ ድረስ እስራኤል በባህረ ሰላጤው አገራት ምንም አይነት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አልነበራትም።
ኢራን በቀጠናው ያላት ተጽእኖ ፈጣሪነት፤ የእስራኤል እና የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች የጋራ ስጋት በመሆኑ ሁለቱን አገራት ሳያቀራርብ አልቀረም ተብሏል።
ፕሬዝደንት ትራምፕ ስምምነቱን ይፋ ሲያደርጉ፤ በምላሹ ኔታኒያሁ በሂብሩ ቋንቋ "ታሪካዊ ቀን" ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ
በአሜሪካ የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች አምባሳደር የሆኑት ዩሱፍ አል ኦታኢባ በበኩላቸው "ለቀጠናው የዲፕሎማሲ ድል ነው" ብለዋል።
ይህ የሁለቱ አገራት ስምምነት የፍልስጤም መሪዎችን ያስደሰተ አይመስልም። የፍልስጤም ከፍተኛ አመራሩ ሃናን አሽራዊ ስምምነቱን በመተቸት አረብ ኤሜሬቶች ከእስራኤል ጋር ስታደርገው የነበረው ድብቅ ስምምነት ጋሃድ ያወጣ ብለዋል።
ፍልስጤማውያን የሁለቱ አገራት የሰላም ስምምነት በዓለም አቀፍ ደረጃ ሉዓላዊ አገር የመሆናቸውን ተስፋ እንደሚያጨልም ስጋታቸውን እየገለጹ ነው።
በቀጣዮቹ ሳምንታት የእስራኤል እና የአረብ ኤሜሬቶች ልኡካን የሁለትዮሽ ስምምነት እንደሚፈርሙ ተነግሯል።
የሁለትዮሽ ስምምነቱ ላይ የኢንቨስትመንት፣ የቴክኖሎጂ፣ የኢነርጂ፣ የባህል፣ በሁለቱ አገራት ኤምባሲዎች መከፍት እና የሁለቱ አገራት ጥቅም ላይ ያተኮረ እንደሚሆነ የሶስቱ አገራት መሪዎች በሰጡት የጋራ መግለጫ ላይ ተገልጿል።
ከዚህ ቀደም ከእስራኤል ጋር መሰል የሰላም ስምምነት የፈረሙት አረብ አገራት ግብጽ እና ጆርዳን ብቻ ናቸው።















