ጃዋር መሐመድ ፡ ፍርድ ቤቱ የእነ አቶ ጃዋርን የዋስትና መብት ጥያቄ ውድቅ አደረገ

የፎቶው ባለመብት, Yadi Pictures, BBC, Hamza Borana/Facebook
የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ አራዳ ምድብ ተረኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት በእነ አቶ ጃዋር የቅድመ ምርመራ መዝገብ ላይ የቀረበውን የዋስትና መብት ውድቅ አደረገ።
አቃቤ ሕግ የቅድመ ምርመራ ምስክሮችን አሰምቶ በመጨረሱ ፍርድ ቤቱ ክስ የሚመስርትበትን ጊዜ ለመስጠትና ተጠርጣሪዎች ባቀረቡት አቤቱታ ላይ ትዕዛዝና ውሳኔ ለማስተላለፍ ነበር ለዛሬ ቀጠሮ የያዘው።
ፍርድ ቤቱ በነሐሴ 29/2012 ዓ.ም በዋለው ችሎት አቃቤ ሕግ ክስ ለመመስረት፣ የቅድመ ምርመራ ግልባጭ ከደረሰው በኋላ በ15 ቀናት ውስጥ ክስ እንደሚመሰርት ያመለከተ ሲሆን፣ ጠበቆች በበኩላቸው የቅድመ ምርመራ ከተጠናቀቀበበት ቀን ጀምሮ ባሉት 15 ቀናት ውስጥ ክስ ይመስርት በማለት ተከራክረዋል።
በዛሬው ችሎት አቃቤ ሕግ ከ1 እስከ 10 ባሉ ተጥረጣሪዎች ማለትም በአቶ ጀዋር መሐመድ፣ በአቶ በቀለ ገርባ፣ በአቶ ያለምወርቅ አሰፋ፣ በአቶ ጌቱ ተረፈ፣
በአቶ ታምራት ሁሴን፣ በአቶ በሽር ሁሴን፣ በአቶ ሰቦቃ ኦልቀባ፣ በአቶ ኬኔ ዱሜቻ፣ በአቶ ዳውድ አብደታ እና በአቶ ቦጋለ ድሪሳ ላይ እስከ መስከረም 8/ 2013 ዓ.ም ድረስ ክስ እንዲመሰርት ወስኗል።
የቅድመ ምርመራ ግልባጭም ለዐቃቤ ሕግና ጠበቆች ከጳጉሜን 2/2012 እስከ ጳጉሜን 5/2012 ዓ.ም ድረስ እንዲሰጣቸው ፍርድ ቤቱ አዟል።
በሌላ በኩልበእነ አቶ ጃዋር ቅድመ ምርመራ መዝገብ ከ11-14 ባሉት ተጠርጣሪዎች፤ በአቶ ሐምዛ አዳነ፣ በአቶ ሸምሰዲን ጣሃ፣ በአቶ ቦና ቲብሌና በአቶ መለሰ ድሪብሳ ላይ ዐቃቤ ሕግ ማስረጃ አቅርቦ ስላላሰማ ክስ የሚኖረው ከሆነ በአምስት ቀናት ውስጥ እንዲያቀርብ ፍርድ ቤቱ ትእዛዝ ሰጥቷል።
የዋስ መብት
ፍርድ ቤቱ በነሐሴ 29/2012 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተጠርጣሪዎችና ጠበቆቻቸው የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅላቸው ችሎቱን ጠይቀው ነበር።
በተለይ ጠበቆች "ወንጀል እንደፈፀሙ የሚያሳይ ነገር እስከሌለ ድረስ ተጠርጣሪዎች እስር ቤት መመላለስ የለባቸውም። የዋስ መብት ሊጠበቅላቸው ይገባል" በማለት አቤቱታቸውን አቅርበዋል።
በሌላ በኩል ዐቃቤ ሕግ ግለሰቦቹ የተጠረጠሩበት ወንጀል ከ15 ዓመት በላይ ሊያስቀጣ የሚያስችል በመሆኑ የዋስ መብታቸው ሊጠበቅላቸው አይገባም በማለት ተከራክሯል።
ፍርድ ቤቱም በዚሁ ችሎት የተጠርጣሪዎችና ጠበቆቻቸው ያቀረቡትን የዋስ መብት ጥያቄ ውድቅ በማድረግ እስከ መስከም 8/2013 ዓ.ም እስር ቤት እንዲቆዩ አዟል።
የፍርድ ቤት ትዕዛዝ አልተተገበረም
የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ አራዳ ምድብ ተረኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት በነሐሴ 29/2012 ዓ.ም በዋለው ችሎት አቶ ጃዋር መሐመድ እና አቶ በቀለ ገርባ ለየብቻቸው መታሰራቸውን ለፍርድ ቤት አመልክተው፤ ማረሚያ ቤቱ ለየብቻቸው መታሰራቸው ተገቢ እንዳልሆነ በመግለጽ አንድ ለይ እንዲሆኑ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር።
ይሁንና ይህ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተግባራዊ እንዳልሆነ ተጠርጣሪዎችና ጠበቆቻው ተናግረዋል።
አቶ ጃዋር መሐመድ "ፖሊሶች ሊተባበሩን ይፈልጋሉ፤ ነገር ግን ከላይ ባለባቸው ጫና ምክንያት ትዕዛዙን ተግባራዊ ማድረግ አልቻሉም። ፖሊስ ትዕዛዙን ለመፈፀም የፍርድ ቤት ድጋፍ ያስፈልጋገዋል" በማለት ተናግረዋል።
በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር የተጠርጣሪዎች ቆይታ ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮማንደር የኔነሽ ገ/እግዚአብሔር፣ "ትዕዛዙን የበላይ ዳይሬክተር ነው የተቀበለው። ለምን እንዳልተፈፀመ ግን ምክንያቱን አላውቀውም" በማለት በችሎቱ ላይ ተናግረዋል።
ፍርድ ቤቱም የፌደራል ፖሊስ ማረሚያ ቤቶች አስተደደርና ጉዳዩ የሚመለከተው ክፍል ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ትዕዛዙን እንዲፈጽሙ እና የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንም አፈጻጸሙን ረፖርት እንዲያርግ አዟል።
በችሎት ላይ ምን ተባለ?
በዛሬው ችሎት ላይ አቶ ጃዋር ምስጋና ማቅረብ እንደሚፈልጉና ለመንግሥትም መልዕክት እንዳላቸው የተናገሩ ሲሆን፣ ለዳኞችና ለፖሊስ ምስጋና አቅርበዋል።
የመናገር መብታቸው እንደተጠበቀላቸውና ፖሊሶችም ጥሩ እንክብካቤ እያደረጉላቸው እንደሆነ ጨምረው ተናግረዋል።
" ይኹን እንጂ ይህ እንክብካቤ ለታዋቂ ሰዎች ብቻ ሳይሆን፤ ለሁሉም ሰዎች መሆን እንዳለበት በማንሳት በሌሎች ስፍራዎች ደንብ ልብስ የለበሱት ፖሊሶች "ሰዎችን እየገደሉ ነው" በማለት ተናግረዋል።
አክለውም " እኛ የፖለቲካ ታሳሪዎች ነን፤ ገድለን፣ ሰርቀን ወይንም ዘርፈን አይደለም እዚህ የተገኘነው፤ የታሰርነው ለኦሮሞ ሕዝብ ስለታገልን ነው" ያሉት አቶ ጃዋር፣ የፍትህ አካላትም፣ ፍትህ ከፖለቲካ ሥልጣንና ከፖለቲካ ድርጅት በላይ እንዲሆን እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በሌላ በኩል አቶ በቀለ ገርባ "በእስካሁኑ ቆይታ ለፍርድ ቤቱ፣ ለአቃቢያነ ሕግ እና ለፖሊሶች ክብር አለን" ብለዋል።
" የፖለቲካ ሰዎች ተመርጠው የዋስ መብት የማያሰጥ አንቀጽ እየተፈለገባቸው እየተከሰሱ ነው" ያሉት አቶ በቀለ መንግሥት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር መወያየት እንዳለበት ተናግረዋል።
















