የፍርድ ቤት ውሎ፡ አቶ ጀዋር መሐመድ በመልካም ጤንነት ላይ ይገኛሉ-ጠቅላይ አቃቤ ሕግ

የፎቶው ባለመብት, Facebook
የፌደራል አቃቤ ሕግ ትናንት ከሰዓት በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ፊት የቀረቡትን አቶ ጃዋር መሐመድን በሚመለከት መግለጫ አውጥቷል።
የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በአቶ ጃዋርና በስምንት ተጠርጣሪዎች ላይ አቃቤ ሕግ የቀዳሚ ምርመራ ምስክሮችን ለማሰማት ቀጠሮ ቢይዝም አቶ ጃዋር መሐመድ አሞኛል በማለታቸው መስተጓጎሉን ገልጿል።
አቶ ጃዋር በከባድ ወንጀል ተጠርጥረው በሕግ ቁጥጥር ስር ያሉ መሆናቸውን የገለፀው መግለጫው ጤናቸውን ለመጠበቅ ባለው አሰራር አስፈላጊውን የጤና ክትትል እና አገልግሎት የሚያገኙ እና እያገኙ ያሉ መሆናቸውን በመጥቀስ "ጤናቸው በመልካም ሁኔታ ላይ ይገኛል" ሲል ገልጿል።
በትናንትናው ዕለት የፌደራል ፖሊስ ባወጣው መግለጫም አቶ ጀዋር መሀመድ ታመዋል፣ ችግር ደርሶባቸዋል በማለት በተለያዩ የሚዲያ አውታሮች የሚወራው ሐሰተኛ መረጃ መሆኑንና በተሟላ ጤንነት ላይ የሚገኙ መሆኑን ገልጿል።
የፌደራል ፖሊስ አክሎም "በሀሰተኛ ወሬ የፍርድ ሂደቱን ለማዛባት የሚደረገው ጥረት በማንኛውም ሁኔታ ተቀባይነት የሌለው ተግባር" ሲል ገልጾታል።
በአቶ ጃዋርና ሌሎች ስምንት ተጠርጣሪዎች ላይ በትናንትናው ዕለት ምስክሮችን ለመስማት ለሶስተኛ ጊዜ ተለዋጭ ቀጠሮ እንደተሰጠ ይታወሳል።
የአቃቤ ሕግ በመግለጫው አቶ ጃዋር ምስክሮችን የማሰማት ሂደት እንዳይጀመር የተለያዩ ምክንያቶች እያነሱ መከራከራቸውን፣ በክርክሩም ላይ የፍርድ ብይን ተሰጥቶ ምስክር መስሚያ ሰዓት ሲደርስ ወጣ ገባ ማለታቸውን ጠቅሶ ድርጊቱን "የምስክሮችን የማሰማት ሂደቱን ለማስተጓጎል እና በግብረአበሮቻቸው ሁከት እና አመጽ ለመቀስቀስ ነው" ብሎታል።
መግለጫው አክሎም የተጠርጣሪው ግብረ አበሮች በተለያዩ መንገዶች ምስክሮችን በማስፈራራት የፍትህ ሂደቱ እንዲስተጓጎል ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ መሆኑን መታወቁንም አስፍሯል።
የትናንት የእነ አቶ ጃዋር ችሎት ውሎ ምን ይመስል ነበር
በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ትናንት ከሰዓት የቀረቡት አቶ ጃዋር መሐመድ መታመማቸውን ለችሎቱ ገለፁ።
ችሎቱ ትናንት ቀጠሮ የያየዘው በእነ አቶ ጃዋር መሀመድ መዝገብ የቅድመ ምርመራ ጉዳያቸው እየታየ ያሉ 14 ተጠርጣሪዎች ላይ አቃቤ ሕግ ምስክሮቹን ለማድመጥ እንዲሁም ችሎቱ ባለፈው ሳምንት ያሳለፋቸውን ትዕዛዞች አፈጻጸም ለመስማት ነበር።
ባለፈው ሳምንት ፍርድ ቤቱ 14ቱም ተጠርጣሪዎች የኮቪድ-19 ምርመራ ተደርጎላቸው ውጤታቸው እንዲቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር።
ትናንት ለችሎቱ የአምስት ተጠርጣሪዎች ውጤት የቀረበ ሲሆን ጌቱ ተረፈ፣ በሽር ሁሴን፣ ኬኔ ዱኔቻ፣ ሰቦቃ ኦልቀባ፣ ዳዊት አብደታ ኮቪድ-19 እንደተገኘባቸው የሚያረጋግጥ ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተጻፈ ባለ ሁለት ገጽ ደብዳቤ ቀርቧል።
የጃዋር ጠባቂ ከነበረው መካከል አንዱ ታምራት ሁሴን ኮቪድ-19 እንደተገኘበት ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ አሳውቋል።
በሌላ በኩል ፍርድ ቤቱ የተቀሩት ዘጠኝ ተጠርጣሪዎች የኮሮናቫይረስ ምርመራ ውጤት እንዲቀርብ ከዚህ በፊት ማዘዙን አስታውሶ ፖሊስ ይህንን ውጤት በቀጣይ የፍርድ ቤት ቀጠሮ ይዞ እንዲቀርብ የቃል ትዕዛዝ ሰጥቷል።
አቶ ጃዋር መሐመድ "በጣም እያመመኝ ነው፤ እዚህ መቆየት አልችልም፤ ፖሊሶች ከ30 ደቂቃ በላይ አትቆይም ብለውኝ ነው የመጣሁት፤ ከተቻለ ፍርድ ቤቱ አሁኑኑ ያሰናብተኝ[ወደ ማረፊያ ቤት]" ሲሉ ለፍርድ ቤቱ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።
በተጨማሪም መቀመጥ እንዳልቻሉ እና ወደ ውጪ ወጥተው እረፍት እንዲያደርጉ ጠይቀው ችሎቱ በመፍቀዱ ወደ ውጪ ወጥተው አየር እንዲወስዱ ተደርጓል።
ከዚህ በተጨማሪም አቶ ጃዋር በውጪ አገር የሚገኙ ባለቤታቸውንና ልጃቸውን "በቪዲዮ ኮንፍረንስ ማናገር እፈልጋለሁ ይህም ይፈቀድልኝ፤ ባይሆን ወጪውን እራሴ እሸፍናለሁ" ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል።
አቶ ጃዋር አክለውም የሕክምና አገልግሎት በራሳቸው ሐኪም እንዲሰጣቸው እንዲደረግ ለችሎቱ ጥያቄ አቅርበዋል።
በሌላ በኩል አቶ ሐምዛ አዳነ (ሐምዛ ቦረና) በጣም እያሳላቸው መሆኑን እና የኮሮናቫይረስ ምልክት እየታየባቸው መሆኑን በመጥቀስ፤ በተደጋጋሚ ምርመራ ለማግኘት ቢጠይቁም እስካሁን ምርመራ እንዳልተደረገላቸው በመግለጽ ፍርድ ቤቱ የኮቪድ-19 ምርመራ እንዲደረግላቸው ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጥያቄ አቅርበዋል።
በተጨማሪም የደም ግፊትና የስኳር ህመምተኛ መሆናቸውን በመጥቀስ ለእነዚህ ህመሞች ሕክምና እንዲያገኙ ሁኔታ እንዲመቻችላቸው ጠይቀዋል።
በተለምዶ 3ኛ ተብሎ በሚታወቀው ማረሚያ ቤት የሚገኘው የኦኤምኤን ጋዜጠኛ መለሰ ድሪብሳ በበኩሉ ከሌሎች ታሳሪዎች በተለየ መልኩ በስልክ ቤተሰቦቻችንን እንዳናገኝ ተደርገናል ሲል ቅሬታውን ለፍርድ ቤቱ አሰምቷል።
አቶ በቀለ ገርባ በበኩላቸው መዝገቡ ውስጥ ያሉ ሌሎች ተጠርጣሪዎች ታምመው ክሳቸውን መከታተል ባልቻሉበት ሁኔታ እንዲሁም አቶ ጃዋር እየታመሙ ችሎት ለመከታተል እየተቸገሩ፣ በታሰሩበት ስፍራ ጠበቆቻቸውን በሚያገኙበት ስፍራ የደህንነት ካሜራ በመገጠሙ ከጠበቆቻቸው ጋር በሚስጥር ማውራት አለመቻላቸውን በመጥቀስ አቃቤ ሕግ ምስክሮቹን እንዳያሰማ፣ ለሌላ ጊዜ ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
የተጠርጣሪዎች ጠበቆች በበኩላቸው ደንበኞቻችንን ለማግኘት በማረሚያ ቤቱ በተገኘንበት ወቅት ወደ ፍርድ ቤት ሄደዋል ተብለን ሳናገኛቸው ቀርተናል፣ እንዲሁም ደግሞ የደህንነት ካሜራው ምስላችንና ድምጻችንን የሚቀርጽ በመሆኑ እንዲስተካከል ፖሊስን ብንጠይቅም ፖሊሶቹ ከአቅማቸው በላይ መሆኑን በመግለጽ ሊያስተካክሉልን አልቻሉም። ስለዚህ ከደንበኞቻችን ጋር በሚስጥር ማውራት የምንችልበት ሌላ ክፍል ይሰጠን ወይንም ደግሞ ካሜራው ይነሳ በማለት ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።
አክለውም ከደንበኞቻቸው ጋር ስላልተወያዩ የአቃቤ ሕግ ምስክር የመስማት ሂደት ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ጠይቀዋል።
አቃቤ ሕግ ስለካሜራው መረጃ እንደሌለውና እንደሚያጣራ በመግለጽ ተጠርጣሪዎችና ጠበቆቻቸው ምስክሮች እንዲጉላሉ እና ተስፋ እንዲቆርጡ እያደረጉ መሆኑን እንዲሁም የችሎቱን ጊዜ እያጓተቱ መሆኑን በመጥቀስ ምስክሮች እንዲሰሙ ችሎቱን ጠይቋል።
ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ ለተቀሩት ዘጠኝ ተጠርጣሪዎች የኮሮናቫይረስ ምርመራ እንዲደረግ፣ እንዲሁም የጤና ጥበቃ በሚያዘው መሰረት ርቀታቸውን ጠብቀው ቤተሰቦቻቸውን፣ ጠበቆቻቸውንና የኃይማኖት አባቶቻቸውን እንዲያገኙ አንዲደረግ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ትዕዛዞቹ ካልተፈፀሙም ፍርድ ቤቱ የራሱን እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል።
በተጨማሪም አቶ ጃዋር መሐመድም ሆኑ አቶ ሐምዛ ቦረና ሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ትዕዛዝ ሰጥቷል። አቶ ጃዋር መሐመድ ልጃቸውና ባለቤታቸውን እንዲያነጋግሩ ሁኔታቸውን እንዲመቻችላቸው ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
አቶ ጃዋር መሐመድ እያመማቸው መሆኑን በመናገራቸውና በተደጋጋሚ ችሎቱን በማቋረጥ እየወጡ በመሆኑ የአቃቤ ሕግ ምስክሮችን ለመስማት አልቻልንም በማለት ለሐሙስ ነሐሴ 14 2012 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል።
















