ብልጽግና ፡ የአቶ ሽመልስ አብዲሳ ንግግር "የግለሰብ እንጂ የብልጽግና አቋም አይደለም"

አማራ ብልጽግና ፓርቲ ላለፉት ሁለት ቀናት በክልሉና በአገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት ሲያካሂድ ቆይቷል። ውይይቱን መጠናቀቅ ተከትሎ ትላንት ምሽት የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አገኘሁ ተሻገር መግለጫ ሰጥተዋል።
የሕግ የበላይነት፣ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ፣ የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ አደረጃጀት፣ የክረምት ሥራዎች ግምገማ፣ የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ ስለተፈጠሩት ጉዳዮችና የአቶ ሽመልስ አብዲሳ ንግግር በውይይቱ መነሳታቸውን አስታውቀዋል።
የሕግ የበላይነትን በማስከበር ረገድ በክልሉ በሕገ ወጥ አደረጃጀት ስር የነበሩትን እንዲፈርሱ መደረጉን ተናግረዋል።
በዚህም በሕግ የሚፈለጉ ሰዎችን ለህግ እንዲቀርቡ የተደረገ ሲሆን በአጠቃላይ የክልሉ ሠላም በጥንካሬ ተነስቷል ብለዋል አቶ አገኘሁ።
"ክልሉ የተሟላ ሠላም ላይ ነው" ያሉት ኃላፊው "ሠላሙ ወደ ኋላ እንዳይመለስ ከሕዝቡ ጋር በጋራ እንሠራለን" ሲሉ ተናግረዋል።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭት በክልሉ እየጨመረ መሆኑን ጠቅሰው የምርመራ አቅምን ከማሳደግ ጀምሮ ሥራዎች መከወናቸውን አስታውቀዋል።
ሆኖም እየታየ ያለው መዘናጋቱ ዋጋ እንዳያስከፍል የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ግድያና መፈናቀል
የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የተፈጸመውን ግድያና መፈናቀል በጉባኤው ላይ ተነስቶ መወገዙን አመልክተዋል።
"ማንም ሰው እንዲሞት አንፈልግም" ያሉት አቶ አገኘሁ "ለሞቱት እና ለፍትህ ነው የምንታገለው" ሲሉ አስረድተዋል።
የድርጊቱ ተሳታፊዎችን ለሕግ በማቅረብ ረገድ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ላደረገው ሥራና ችግሩ እንዳይባባስ ለሠሩ ወጣቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች እንዲሁም የሐይማኖት አባቶች ፓርቲው ባደረገው ውይይት ላይ እውቅና መሰጠቱንም ጠቁመዋል።
በቀጣይም አጥፊዎች ወደ ሕግ እንዲቀርቡና አስፈላጊው እርምጃ እንዲወሰድባቸው ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ጋር በጋራ እንደሚሠሩ አስታውቀዋል።
የተፈናቀሉና ቤት ንብረት የወደመባቸውን ሰዎች ለማቋቋም የጀመርነውን ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አውስተዋል።
የፓርቲው ጉባኤ ቀደም ሲል ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረትም ከክልሉ ውጪ የሚኖሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች በሚኖሩበት አካባቢ እንዲወከሉ፣ በቋንቋቸው እንዲማሩና እንዲዳኙ ለመሥራት ባቀደው መሠረት ይህንን ለማሳካት ከሌሎች ክልሎች ጋር በጋራ እንሠራለንም ብለዋል።
የአቶ ሽመልስ አብዲሳ ንግግር
አቶ አገኘሁ በፓርቲው ጉባኤ ላይ በቅርቡ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ቀደም ባላ ጊዜ አደርገውታል በተባለ ንግግር ዙሪያ በኮንፈረንሱ ላይ ውይይት ተደርጎበታል።
"አንደኛ ጉዳዩ የተነገረው መቼም ይሁን መቼ ለምን አሁን ማውጣት አስፈለገ? የሚለው አነጋግሮናል። የሁለተኛ ንግግሩ በይዘቱ ስህተት ነው" ሲሉ ገልጸዋል።
ጨምረውም በርዕሰ መስተዳደሩ ንግግር ላይ የተንጸባረቀው ሃሳብ "የግለሰብ አቋም ነው። የፓርቲያችን የብልጽግና አቋም አይደለም" ሲሉ ተናግረዋል።
በውይይቱም የንግግሩ ይዘት በብልጽግና ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ደረጃ በዝርዝር መገምገም እንዳለበትና የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ አቅጣጫ መቀመጡንም አመለክተዋል።
"ኮንፈረንሱ የተሰጠው መግለጫው ትክክል አለመሆኑን፤ በይዘት ደረጃ ስህተት መሆኑን ገምግሟል። የይቅርታ መጠየቅ የግለሰብ ጉዳይ ነው። የፓርቲ አቋም ግን አይደለም" ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል አቶ አገኘሁ።
በክልሉ የአመራር መከፋፈል አለመኖሩን እና አንድነቱ የጠነከረ ለአማራ ህዝብ እየሠራ ያለ አመራር መኖሩን ጠቅሰው "በንግግሩም ላይ ምንም ዓይነት የሃሳብ ልዩነት የለም" ሲሉ በጉዳዩ ላይ የአማራ ክልል አመራሮች ልዩነት አላቸው ይባላል ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሻቸውን ሰጥተዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ባሕር ዳር መገኘት
ረቡዕ በውይይቱ የመጨረሻ ዕለት በባሕር ዳር ከተማ የተገኙት የፓርቲው ፕሬዝዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በኮንፈረንሱ ላይ ቀደም ሲል በተያዘ ፕሮግራም እንደተገኙ አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የ5 ቢሊዮን ችግን ተከላ ፕሮግራምን መጠናቀቅ ከማብሰር በተጨማሪ የኮንፈረንሱን የማጠቃለያ አቅጣጫና የሥራ መመሪያ አስቀምጠዋል ብለዋል።
የትግራይ ክልል ምርጫ
የትግራይ ክልል ምርጫ ለማካሄድ ወስኖ መንቀሳቀሱ ፀረ ሕገ መንግሥት እንቅስቃሴ ነው ያሉት አቶ አገኘሁ "ሕገወጥ ምርጫ በመሆኑ ፌደራል መንግሥት እርምጃ ይውሰድ ነው የእኛ አቋም" ብለዋል።
"የአማራ ክልል የትግራይ ክልልን ለምን ምርጫ ታካሂዳለህ ማለት አይችልም። የፌደሬሽን ምክር ቤትና ምርጫ ቦርድ እውቅና ስለነፈገው የፌደራል መንግሥት ማድረግ የሚችለውን ያደርጋል።"
"የራያና ወልቃይት ሕዝቦች አማራ ማንነት ያላቸው ሲሆኑ ምርጫወንም አልደገፉትም። ባለመደገፋቸውም በአሁኑ ሰዓት እየታሰሩና እየተሰደዱ ተፈናቃዮችን እያስተናገድን ነው" ብለዋል።
"የእነዚህን ሰዎች ጥያቄ የፌደራል መንግሥቱ መስማት አለበት። ጣልቃ ገብቶም ማስተካከልም አለበት። ከዚያ ውጪ የትግራይ ክልል ምርጫ ስላካሄደ ብለን እኛ አንተነኩስም። እኛ ከትግራይ ህዝብ ጋር በሰላም ነው መኖር የምንፈልገው" ሲሉ አስረድተዋል።
ጨምረውም ከትግራይ ወንድም ሕዝብ የአማራን ሕዝብ ህወሐት ሊነጥለው አይችልም በማለት ገልጸዋል።
"የአማራን ሕዝብ ከሌሎች ሕዝቦች ጋር ለማጋጨትና ለመነጠል የሚሰሩ ህወሓት እና ኦነግ-ሸኔን የመሳሰሉ ኃይሎችን ከሌሎች ወንድም ሕዝቦች ጋር በመተባበር መታገል እንደሚገባም ተግባብተናል" ሲሉ ሃሳባቸውን አጠናቀዋል።















