ነፍስ በማጥፋት ወንጀል ለ27 ዓመት እስር ቤት የማቀቀው ቻይናዊ ነፃ ነህ ተባለ

በቤይዢንግ የሚገኝ እስር ቤት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በምስራቅ ቻይና በግድያ ወንጀል 27 ዓመት ተፈርዶበት የነበረው ቻይናዊ ነፃ ነህ ተብሎ ተለቀቀ።

ዛንግ ዩሃን እ.ኤ.አ በ1993 ሁለት ልጆችን በመግደል ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር በዋለበት ወቅት ፖሊስ ጥፋቱን እንዲያምን እንዳሰቃየውና እንዳስገደደው ተናግሮ ነበር።

ዛንግ በቻይና ለ9778 ቀናት፤ በዢያንግዢ ማረሚያ ቤት በስህተት ለረዥም ጊዜ የታሰረ ሰው ሆኖ ተመዝግቧል።

የዛንግን የክስ መዝገብ ዳግም ያንቀሳቀሱት አቃብያነ ህጎች በወቅቱ የሰጠው የእምነት ክህደት ቃል ወጥነት ይጎድለው እንደነበር በመግለጽ ከተፈፀመው ወንጀል ጋርም እንደማይገናኝ ተናግረዋል።

ከፍተኛው ፍርድ ቤት ጥፋተኛ ተብሎ 27 ዓመት በእስር ቤት ውስጥ ላሳለፈበት ወንጀል በቂ ማስረጃ የለም ብሎ በመወሰኑ በነጻ ተለቅቋል።

ታዛቢዎች ቻይና በወንጀል ተጠርጥረውና በስህተት ተፈርዶባቸው በእስር ቤት የሚገኙ ሰዎችን ለመልቀቅ ፈቃደኝነት እያሳየች ነው ሲሉ ተናግረዋል። ይህ ግን የፖለቲከኛ እስረኞችን አይጨምርም ተብሏል።

በቻይና መገናኛ ብዙኀን የቀረበው ምስል እንዳሳየው ዛንግ ከእስር ቤት ከወጣ በኋላ ከ83 ዓመት እናቱ ጋርና ከቀድሞ ባለቤቱ ጋር ተገናኝቷል።

በቻይና ፖሊስ በተለያዩ ወንጀሎች የተጠረጠሩ ሰዎች ላይ ምርመራ በሚያደርግበት ወቅት ድብደባ እንደሚፈጽም፣ እንደሚያሰቃይ፣ እንቅልፍ እንደሚከለክል፣ በሲጋራ እንደሚያቃጥል፣ ይነገራል።

ከዚህ ቀደም በወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎች በዚህ ሁሉ ውስጥ አልፈው የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ ይደረግ ነበር።

እ.ኤ.አ በ2010 ግን የቻይና የሕግ ስርዓት አስገዳጅ የሆነን ምርመራ ለማስቀረት መስራት ጀመረ።

የሞት ፍርድም ቢሆን በቻይና ጠቅላይ ፍርድ ቤት መጽደቅ ያለበት ሲሆን የተፈፀመ ወንጀል ላይ የሚሰጥ ፍርድም በተጠርጣሪው የእምነት ክህደት ቃል ላይ ብቻ እንዳይመሰረት ተወስኗል።

Grey line

ዛንግ ከቀድሞ ሚስቱ፣ ሶንግ ጋር ከመለያየታቸው በፊት ሁለት ወንድ ልጆች ወልደዋል። ሶንግ ድጋሚ ብታገባም የቀድሞ ባለቤቷን ይግባኝ ክስ ግን ትከታተልና ትደግፍ ነበር።

"የችሎቱን ውሳኔ ስሰማ በጣም ነው ደስ ያለኝ" ብላለች ሶንግ። ዛንግ በእስር ቤት ላባከናቸው ዓመታት ካሳ እንደሚከፈለው ችሎቱ ወስኗል።

"ከደንበኛዬ ጋር ስለ ካሳው መጠን እንነጋገርበታለን" ብለዋል የዛንግ ጠበቃ፣ ዋንግ ፌይ ለቻይና ዴይሊ።

አክለውም "እንዲህ ዓይነት የሕግ ጥሰት የፈጸሙትንም ተጠያቂ ለማድረግ እቅድ አለን።"

ዛንግ በቁጥጥር ስር የዋለው እ.ኤ.አ በ1993 ሲሆን ሁለት ወጣቶች በናንቻንግ ግዛት ጂያንግዢ ከተማ በውሃ ኩሬ ውስጥ አስከሬናቸው መገኘቱን ተከትሎ ነው።

ዛንግ የሟቾቹ ጎረቤት ሲሆን በወቅቱ በግድያ ወንጀል ተጠርጥሮ ነበር በቁጥጥር ስር የዋለው።

በ1995 የናንቻንግ ፍርድ ቤት ጥፋተኛ ነህ በማለት ሞት የፈረደበት ቢሆንም ነገር ግን ፍርዱ ሁለት ዓመት ከታሰረ በኋላ በእድሜ ይፍታህ ተቀይሮለታል።

ዛንግ በምርመራ ወቅት ስቃይ እንደደረሰበት በመግለጽ ነጻ መሆኑን ሲከራከር ነበር።

ነገር ግን በወቅቱ ይግባኝ ያለው ጉዳይ ውጤት ሳያስገኝለት ቀርቷል። ከዚያ በኋላ በ2019 መጋቢት ወር ላይ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ጉዳዩን ዳግም ለማየት ተስማምቶ ዛንግ በቂ ባልሆነ ማስረጃ እስር ቤት መወርወሩን በመግለጽ ነፃ ነህ ብሎታል።

ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ ቲያን ጋንሊን እንዳሉት "ያገኘናቸውን ማስረጃዎች ከፈተሽን በኋላ የዛንግን ወንጀል የሚያስረዱ ቀጥተኛ ማስረጃዎች ማግኘት አልቻልንም። ስለዚህ አቃቢያነ ህጎቹ ያቀረቡትን ሃሳብ ተቀብለን ዛንግን ነፃ መሆኑን የሚገልጽ ውሳኔ አሳልፈናል።"

በ1993 ሁለቱን ወጣቶች ማን እንደገደላቸው እስካሁን ድረስ አልታወቀም።