ቦይንግ 737 ማክስ በድጋሚ ለመብረር ተቃርቧል ተባለ

ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የአሜሪካ ተቆጣጣሪዎች ከበረራ ውጪ የሆነው አውሮፕላን ዳግም ወደ በረራ ከመመለሱ በፊት ማሟላት ያለበትን ዝርዝሮችን አቀረቡ።

የፌደራል አቪየሽን አስተዳደር (ኤፍኤኤ)ም እንዲሁ አውሮፕላኑ ዳግም ወደ በረራ ከመግባቱ በፊት ማሟላት ያለበትን ዝርዝር ነገሮች ማቅረቡ ተሰምቷል።

737 ማክስ ሁለት አውሮፕላኖች ተከስክሰው የ346 ሰዎች ህይወት ከጠፋ በኋላ ከበረራ ከታገደ ከአንድ አመት በላይ ሆኖታል።

አውሮፕላኑ ሙሉ ሙሉ ከበረራ የታገደው በጎርጎሳውያኑ መጋቢት ወር 2019 ዓ.ም ነበር።

ቦይንግ 737 ማክስ እንዲያሟላ የተጠየቀውን ዝርዝር ነገሮች አሟልቶ በጎርጎሳውያኑ አዲስ አመት ዳግም ወደ በረራ ለመመለስ አቅዷል።

ለውጥ እንዲደረግባቸው ከተገለፁት ነገሮች መካከል የበረራ መቆጣጠርያ ሶፍትዌር (መተግበሪያ)፣ አብራሪዎቹ ማሟላት ያለባቸውን ነገሮች መከለስ እና የውስጥ መስመሮቹን መቀየር ናቸው።

ሰኞ እለት ተያይዞ በወጣ ሪፖርት፣ የአሜሪካ አቪየሽን አስተዳደር (ኤፍኤኤ) ሁለቱ አውሮፕላኖችን እንዲከሰከሱ ያደረጉትን ችግሮች ቦይንግ በበቂ ሁናቴ ማስተካከሉን ገልጿል።

ኤፍ ኤኤ ያቀረበው ምክረ ሃሳብ ይፋ ከሆነ በኋላ እና ቦይንግ ለውጦቹን ካደረገ አውሮፕላኖቹ ለበረራ ዝግጁ ይሆናሉ ተብሏል።

የቦይንግ የዲዛይን ማሻሻያ ለአየር መንገዶች በተጨሸጡት አውሮፕላኖች እንዲሁም ገና ባልታዘዙትና ባልተሰሩት በአጠቃላይ ሊደረግ ይገባል ተብሏል።

"ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ ወደ በረራ ለመመለስ እየሰራን ነው፣ ከኤፍኤኤ እና ሌሎች አለም አቀፍ ተቆጣጣሪዎች ጋር በቅርበት እየሰራን ነው።

" ገና ከፊታችን ብዙ ስራ ይቀረናል፣ ይህ ፈቃድ በማግኘቱ ሂደት ላይ ወሳኙ ምዕራፍ ነው" ሲሉ ለቢቢሲ የተናገሩት የቦይንግ ቃል አቀባይ ናቸው።

ቦይንግ 737 ማክስ በጎርጎሳውያኑ 2021 ላይ ዳግም ወደ በረራ ይመለሳል የሚል ተስፋ ቢያደርግም፣ አየር መንገዶች ግን አሁንም በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እና በተጣለው ገደብ የተነሳ የመንገደኛ ቁጥር ቀንሶባቸዋል።

ሌላው ተቋሙ ሊወጣው የሚገባው ተግዳሮት የአውሮፕላን አብራሪዎች ስልጠና ፕሮግራም መቅረጽ፣ ገለልተኛ በሆነ ወገን የቴክኒክ ፍተሻ ማድረግ እና የምስለ በረራ ውጤት ናቸው።

ቦይንግ ለ737 ማክስ በምስለ በረራ ለአብራሪዎች ስልጠና የሚሰጠው ብሪቲሽ አየር መንገድ በዋናነት በሚገለገልበት የጋትዊክ አውሮፕላን ማረፊያ ነው።

የፌደራል አቪየሽን አስተዳደር ምክረ ሃሳብ ከ18 ወራት በላይ የፈጀ ሲሆን የ40 ኢንጂነሮች፣ ተቆጣጣሪዎች፣ አብራሪዎች፣ እና ቴክኒክ ድጋፍ የሚያደርጉ ሰራተኞች ሃሳብ ተካትቶበታል።

ኤጀንሲው "ጥረቱ የኤፍኤኤ 60 ሺህ ሰዓት የጠየቀ ነው" ብሎታል።

የኤፍ ኤኤ ምክረ ሃሳብ ላይ ለመጨረሻ ጊዜ ውሳኔ ከመሰጠቱ በፊት በህዝብ ለ45 ቀናት ያህል ይገመገማል።