ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሆንግ ኮንግ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ምርጫዋን ለአንድ ዓመት አራዘመች
የኮሮናቫይረስ በመስፋፋቱ ምክንያት የሆንግ ኮንግ መንግሥት በመጪው መስከረም ሊያካሂደው አቅዶት የነበረው የፓርላማ ምርጫን በአንድ ዓመት ማራዘሙን አስታወቀ።
ሆንግ ኮንግ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ የኮሮናቫይረስ በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፋ ሲሆን ዛሬ 121 በበሽታው የተያዙ ሰዎች ተገኝተዋል።
የምርጫውን መራዘም ተከትሎ ተቃዋሚ ፓርቲ መንግሥት ወረርሽኙን እንደ ሰበብ በመጠቀም ሕዝቡ የሚፈልገውን እንዳይመርጥ እያደረገ ነው ሲል ከሷል።
ትናንት የግዛቲቱ መንግሥት 12 የዴሞክራሲያዊ ለውጥ ጠያቂዎች በምርጫው እንዳይወዳደሩ አግዷቸው ነበር።
ተቃዋሚው ፓርቲ ቻይና በግዛቲቱ የጣለችውን አወዛጋቢ የደኅንነት ሕግ ተከትሎ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ መሰረት በማድረግ በፓርላማው ውስጥ በርካታ መቀመጫዎችን ለማግኘት ተስፋ አድርጎ ነበር።
እነዚህ የዴሞክራሲ ለውጥ አራማጆች ባለፈው ዓመት በተካሄደው አካባቢያዊ ምርጫ ላይ ከ18 ምከር ቤቶች 17ቱን ለማሸነፍ ችለው ነበር።
የሆንግ ኮንግ ዋና አስተዳዳሪ የሆኑት ካሪ ላም የምርጫውን ጊዜ ለማራዘም የአስቸኳይ ጊዜ የማወጅ ሥልጣናቸውን ሊጠቀሙ እንደሚችሉ አስታውቀው፤ "ባለፉት ሰባት ወራት ውስጥ ከሰጠሁት ውሳኔዎች ሁሉ ይህ እጅጉን አስቸጋሪ ውሳኔ ነው" ብለዋል።
ሆንግ ኮንግ ውስጥ የወረርሽኙ ሁኔታ ከዕለት ዕለት እየተበራከተ ሲሆን ባለፉት አስር ቀናት ውስጥ በተከታታይ በየዕለቱ ከ100 በላይ በበሽታው የተያዙ ሰዎች እየተመዘገቡ መሆኑ አሳሳቢ ሆኗል።
በሆንግ ኮንግ ውስጥ እየተመዘገበ ያለው የህሙማን ቁጥር ዝቅተኛ ቢሆንም ግዛቲቱ በሽታውን ተቆጣጥራው መቆየቷን ተከትሎ በፍጥነት እየጨመረ መምጣቱ ስጋትን ፈጥሯል።
በአሁኑ ጊዜ በግዛቲቱ የታየው የበሽታው መስፋፋት "ለሦስተኛ ጊዜ በሽታው ማገርሸቱን" የሚያመለክት ነው እየተባለ ሲሆን፤ ረቡዕ ዕለት አስተዳዳሪዋ ካሪ ላም የሆንግ ኮንግ ሆስፒታሎች ሊቋቋሙት በማይቸል "የወረርሽኙ ማዕበል ልትመታ" ከምትችልበት ጠርዘ ላይ እንደደረሰች አስጠንቅቀው ነበር።
ሆንግ ኮንግ ከሁለት ሰዎች በላይ በአንድ ስፍራ ላይ መገኘትን የሚከለክለውን ደንብ ተግባራዊ ከማድረግ በተጨማሪ ጥብቅ የቫይረሱ መከላከያ መንገዶችን እንዲተገበሩ አዛለች።