ዶናልድ ትራምፕ በቀጣዩ ዓመት የሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንዲዘገይ ጠየቁ

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በህዳር ወር የሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በፖስታ የሚሰጥ ድምጽ ወደ ማጭበርበርና የተሳሳተ ውጤት ያመራል በሚል ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ጠየቁ።

ምርጫው የሚዘገየው እስከመቼ ድረስ እንደሆነ ሲናገሩም ሰዎች "በአግባቡ፣ ደህንነታቸውና ምስጢራቸው ተጠብቆ" መምረጥ ሲችሉ ብለዋል።

የፕሬዝዳንቱን ንግግር የሚደግፍ መረጃ ያለው አነስተኛ ሲሆን፤ ፕሬዝዳንቱ ለረዥም ጊዜ ግን በፖስታ የሚሰጥ ድምጽ ለማጭበርበር ሊጋለጥ እንደሚችል አጠራጣሪ ሁኔታዎች መኖራቸውን ሲጠቅሱ ነበር።

የአሜሪካ ግዛቶች በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የተነሳ በፖስታ የሚሰጥን ድምጽ ቀላል ለማድረግ ይፈልጋሉ።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ በትዊተር ሰሌዳቸው ላይ "በዓለም ደረጃ በፖስታ የሚሰጥ ድምጽ" በህዳር ወር የሚደረገውን ምርጫ "በጣም ልክ ያልሆነ እና በታሪክ የተጭበረበረ ያደርገዋል" በማለት "ለአሜሪካም ማፈሪያ" ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ስድስት የአሜሪካ ግዛቶች በህዳር ወር የሚካሄደውን ምርጫ በአጠቃላይ "በፖስታ በሚሰጥ ድምጽ" ለማድረግ አቅደው ነበር።

እነዚህ ግዛቶች ዋሺንግተን፣ ኦሪገን፣ ኮሎራዶ፣ ሃዋይ፣ ዩታህ እና ካሊፎርኒያ ናቸው።

እነዚህ ስድስት ግዛቶች ለተመዘገቡ መራጮች ወዲያውኑ በፖስታ ድምጽ መስጫ የሚልኩ ሲሆን፤ ፖስታዎቹም በምርጫ ቀን ተመልሰው የሚላኩ አልያም በምርጫ ጣቢያ የሚመለሱ ይሆናል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በአንዳንድ አስገዳጅ ሁኔታዎች ምክንያት በአካል ድምጻቸውን የሚሰጡ የተወሰኑ ሰዎች ይኖራሉ ተብሏል።

ግማሽ ያህል የአሜሪካ ግዛቶች ለተመዘገቡ መራጮች በጥያቄ መሰረት በፖስታ ድምጽ መስጠትን ይፈቅዳሉ።

በፖስታ ድምጽ መስጠትን የሚቃወሙ አካላት መራጮች በማይመርጡ ተመዝጋቢዎች ምትክ ከአንድ በላይ ደምጽ ሊሰጡ ይችላሉ ሲሉ ይከራከራሉ።

ከዚህ በፊት ፕሬዝዳንት ትራምፕ "በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በአንድ ሰው ሳሎን ቁጭ ብለው የምርጫ ወረቀቶችን ሊሞሉ ይችላሉ" ሲሉ ስጋታቸውን ተናግረው ነበር።

ይሁን እንጂ ለዓመታት በመላ አገሪቱ በተደረገ ጥናት እስካሁን ድረስ እንዲህ እንደሚሰጋው በሰፊው ያጋጠመ ማጭበርበር አልታየም።