በቺካጎ ሁለት የክርስቶፈር ኮለምበስ ሃውልቶች ተነሱ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በአሜሪካዋ ቺካጎ ከተማ ቆመው የነበሩት ሁለት የክርስቶፈር ኮሎምበስ ሃውልቶች በጊዜያዊነት እንዲነሱ ተደረጉ።
ለሳምንታት ዘልቆ በነበረው የተቃውሞ ስለፍ ላይ ሰልፈኞች የጣሊያናዊውን አሳሽ ሃውልት ለማፍረስ ሙከራ ሲያደርጉ ነበር።
ሃውልቶቹ ቆመው ከሚገኙበት ስፍራ የሚነሱት በጊዜያዊነት ነው ቢባልም፤ በሰዎች ቆዳ ቀለም ምክንያት አድልዎ ፈጽመዋል ተብለው ሃውልቶቻቸው እንዲነሱ ከተደረጉት መካከል የክርስቶፈር ኮለምበስ ሃውልት ተካቷል።
የጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድ ግድያ በአሜሪካ እና በመላው ዓለም በፖሊስ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ለማስቆም እና በጥቁር እና ነጭ ሰዎች መካከል እኩልነት እንዲሰፍን የተቃውሞ ስለፎች ተቀጣጥለው ነበር።
በኢሊኖይስ ግዛት የምትገኘው የቺካጎ ከተማ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ በግራንት እና አሪጎ ፓርክ ውስጥ የሚገኙት የክርስቶፈር ኮሎምበስ ሃውልቶች “በጊዜያዊነት . . . ላልተወሰነ ጊዜ ተነስተዋል” ብሏል።
ባሳለፍነው ሳምንት ለተቃውሞ የወጡ ሰዎች በግራት ፓርክ የሚገኘውን ሃውልት ለማፍረስ ጥረት ሲያደርጉ ከፖሊስ ጋር ተጋጭተው ነበር።
የቺካጎ ነዋሪዋ ብሬንዳ አረሜንታ የኮሎምበስ ሃውልት እየተነሳ ባለበት ወቅት “ሃውልቱ ሲወርድ መመልከት ሃሴት ይሰጣል” ስትል ለኤኤፍፒ ዜና ወኪል ተናግራለች።
ሃውልቱ እንዲነሳ የሚፈልጉ ተቃዋሚዎች እንዳሉ ሁሉ ሃውልቶቹ የታሪካችን አካል ናቸው በማለት፤ በሃውልቶቹ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት አጥብቀው የሚያጥላሉ አሜሪካውያን አልጠፉም።
የኮሎምበስ ሃውልቶች ከመፍረሳቸው በፊት በደጋፊ እና ተቃዋሚዎች መካከል የጋል አለመግባባት ተፈጥሮ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, EPA
ባሳለፍነው ወር 3 ሜትር ርዝመት የነበረው እና በሴንት ፖል ሚኒሶታ ግዛት ቆሞ የነበረው የኮለምበስ ሃውልት በተቃዋሚዎች እንዲወድቅ ተደርጎ ነበር።
በቦስተን የነበረው የኮሎምበስ ሃውልት ደግሞ አንገቱ ተቆርጦ ተጥሏል።
አሳሹ ክርሰቶፈር ኮለምበስ በ15ኛው ክፍለ ዘመን “አዲሲቷን ዓለም” ያገኘ አሳሽ ሲባል በትምህርት መጻሕፍት ጭምር ይወዳሳል።
በሌላ በኩል የኮለምበስ ተቺዎች እና ቀደምት የአሜሪካ ነዋሪዎች፤ የኮለምበስ ወደ አሜሪካ መምጣት ቅኝ ግዛትን ያስፋፋ እና የዘር ፍጭት ያስከተለ ነው በማለት ይኮንኑታል።















