ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኡጋንዳ፡ ፖሊስ ከኮሮናቫይረስ በላይ ገዳይ የሆነባት አገር
ኡጋንዳ ውስጥ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የተጣለውን ገደብ ለማስፈፀም በተንቀሳቀሱ የፀጥታ ኃይሎች በተወሰደ ርምጃ ቢያንስ 12 ሰዎች መገደላቸው ተገልጿል።
ነገር ግን እስካሁን ድረስ በኮሮናቫይረስ ምክንያት የሞተ አንድም ሰው የለም። ቢቢሲ በፀጥታ ኃይሎች የቤተሰብ አባላቶቻቸው የተገደሉባቸውን የተወሰኑ ቤተሰቦች አግኝቶ አነጋግሯል።
የ65 ዓመቷ ጆይስ ናሙጋሉ ሙታሲጋ፣ ለስምንት ቤተሰቦቿ የእለት ጉርስ ለማቅመስ ደፋ ቀና የምትለው ብቻዋን ነው። በዚህ ላይ ሁለት የልጅ ልጆቿ የማሳደግ ኃላፊነት ተጭኗታል።
በሰኔ ወር፣ ከሶስት ሳምንታት በፊት፣ ፖሊስ ልጇ ኤሪክ ሙታሲጋን እግሩን በጥይት የመታው ሲሆን ጉዳቱ ለሞት ዳርጎታል።
እንደ እናቱ ገለፃ ከመሞቱ በፊት ወደ ሙላጎ ሆስፒታል ተወስዶ የቀዶ ጥገና ለማድረግ ቢሞከርም ህይወቱን ማትረፍ አልተቻለም።
የ30 ዓመቱ መምህር በፀጥታ አካላት የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የተጣለ ገደብን ለማስከበር በሚንቀሳቀሱ ፖሊሶች በተተኮሰ ጥይት መሞቱ ተነግሯል።
በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት 12 ኡጋንዳውያን የተገደሉት በፖሊሶች፣ ወታደሮች እንዲሁም በታጠቁ የሚሊሻ አባላት እንደሆነ ይታመናል።
ከመጋቢት ጀምሮ ኡጋንዳውያን የተጣለውን ገደብ እንዲያከብሩ ለማድረግ በዋና ዋና መንገዶች ላይ በመንቀሳቀስና መንገዶችን በመዝጋት ክትትል ያደርጋሉ። በእንቅስቃሴ ገደቡ ውስጥ ከተካተቱት በሞተር ብስክሌቶች የሚሰጡ የትራንስፖርት አገልግሎትና ከምሽት እስከ ንጋት ድረስ የተጣለው ሰዓት እላፊ ይገኝበታል።
በርካታ ኡጋንዳውያን የፀጥታ ኃይሎች መንገድ ዘግተው በሚቆጣጠሯቸው ስፍራዎች ላይ ሲደርሱ እንደሚፈሩ ይናገራሉ።
አቶ ሙታሲጋ በሜሪታይም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት አስተማሪ የነበረ ሲሆን፣ ከዋና ከተማዋ ካምፓላ ወጣ ብሎ በሚገኘው መኖሪያ ቤቱ አነስተኛ ሱቅ ነበረው።
አንድ ቀን ፖሊስ እና የአካባቢው ሚሊሻ አባላት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ሲሆን የሰዓት እላፊውን ጥሰዋል ያሏቸውን ሰዎችን በቁጥጥር ስር እያዋሉ ነበር።
የሙታሲጋ ሱቅ ውስጥ ተቀጥሮ የሚሰራ ሰራተኛ ከሱቁ ውጪ በመገኘቱ በቁጥጥር ስር መዋሉን እናቱ ያስታውሳሉ።
"ምህረት እንዲያደርጉለት ፖሊሶቹን ለመንኳቸው፤ ፖሊሶቹ እርስ በእርሳቸው ተጨቃጨቁ" ሲል በወቅቱ ሙታሲጋ ለጋዜጠኞች ተናግሮ ነበር።
ከዚያም ሰዎች እየተሰባሰቡ በኋላ ነገሮች እየተጋጋሉ መጡ። ፖሊስ የተሰባሰቡ ነዋሪዎች ለመበተን በሚል ወደ ሰማይ ተኮሰ፤ ከዚያም ወደ ሰዎቹ ማነጣጠሩን ሙታሲጋ ተናግሮ ነበር።
ከዚህ በኋላ በተተኮሰ ጥይት ሙታሲጋ እግሩን ተመትቷል። "በፍጥነት ሞተር ብስክሌታቸው ላይ ተፈናጥጠው ከአካባቢው ሄዱ" በማለት በወቅቱ ተናግሮ ነበር።
ይህንን የተናገረው ወደ ሆስፒታል እየተወሰደ በነበረበት ሰዓት ነው። ፖሊስ የሙታሲጋን ምስክርነት ቃል አላረጋገጠም።
ቤተሰቦቹ የሙታሲጋ ጉዳት ይድናል የሚል ተስፋ ነበራቸው።
"ሆስፒታሉ ውስጥ ቀዶ ጥገና ተሰርቶለት እስኪወጣ እየጠበቅን ነበር፤ የሆስፒታሉ ባለሙያዎች ጉዳቱ ከፍተኛ በመሆኑ ቀዶ ጥገናውን ማከናወን አለመቻላቸውን ነገሩን" ሲሉ እናቱ ለቢቢሲ ገልፀዋል።
አክለውም ሙታሲጋ ለቀዶ ጥገና በገባበት ሆስፒታል ውስጥ ሕይወቱ ማለፉን ተናግረዋል።
ከሆስፒታል የተገኘው የሞት ምስክር ወረቀት እንደሚያስረዳው ለህይወቱ ማለፍ ምክንያት የሆነው በጥይት መመታቱ ነው።
የሙታሲጋ እናት ልጇን በሞት ከተነጠቀች በኋላ አንዳንዶች ወደ ፍርድ ቤት በመሄድ እንድትከስ እንደ ነገሯት ትናገራለች፤ ነገር ግን "ፖሊሰ ማን ተኩሶ እንደገደለው ለይቶ አላቀረበም፤ ማንን ነው የምከሰው?" ስትል ትጠይቃለች።
በኡጋንዳ የአካባቢ ሚሊሻዎች በእአአ በ2000 ዓ.ም የተቋቋሙ ናቸው። ከዚህ በፊት እነዚህ ሚሊሻዎቹ በርካታ ግድያዎችን መፈፀማቸው ተጠቅሶ ክስ ይቀርብባቸዋል።
ከክሱ በኋላ መንግሥት የበተናቸው ቢሆንም ዳግም በ2008 መልሶ እንዲቋቋሙ አደርጓል።
ሚሊሻዎቹን የሚተቹ አካላት እንደሚሉት በሚገባ ባልሰለጠኑ ወጣቶች እጅ ጠብመንጃ በመግባቱ ለደረሰው ጥፋት ሁሉ ተጠያቂ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ሚሊሻዎቹ አሁን በአጠቃላይ ከግዳጅ ላይ ተጠርተው ዳግም ስልጠና እየወሰዱ ይገኛሉ።
ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒም ሆኑ ሌላ ከፍተኛ ባለስልጣን ግድያዎቹን ቢያወግዙም ቢቢሲ ያነጋገራቸው የደህንንት ኤጀንሲዎች መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
የመብት ተሟጋቾች ችግሩ የመዋቅር መሆኑን በማንሳት ይከራከራሉ።
የደህንነት እና ፀጥታ ባልደረቦቹ የኮቪድ-19 ስርጭትን ለመግታት የተቀመጠው ገደብን ሽፋን በማድረግ ሰብዓዊ መብት ጥሰዋል ሲሉም ይወነጅሏቸዋል።
የሟች ቤተሰቦች ገዳዮችን የፍትህ አደባባይ ለማቅረብ ፈታኝ መሆኑን ቢናገሩም ባለፉት አምስት ወራት ግን ሁለት ጉዳዮች ችሎት ፊት ቀርበው ውጤት አግኝተዋል። ክሶቹ አንድ ወታደርና አንድ ሚሊሻን የሚመለከት ነበሩ።