ሙዚቀኛው ካኒዬ ዌስት ለቀጣዩ የአሜሪካ ምርጫ የምረጡኝ ቅስቀሳውን ጀመረ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
እውቁ አሜሪካዊ ሙዚቀኛ ካኒዬ ዌስት ከ4 ወራት በኋላ በሚካሄደው የአሜሪካ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ላይ ለመሳተፍ ይፋዊ የምረጡኝ ቅስቀሳውን ትናንት ምሽት በደቡብ ካሮላይና ጀመሯል።
የ43 ዓመቱ ካኒዬ ዌስት ‘በርዝደይ ፓርቲ’ የተሰኘ ፓርቲውን ይዞ ነው ወደ ምርጫ ውድድሩ የሚገባው።
አሁንም ቢሆን ግን በርካታ ደጋፊዎቹ ካኒዬ ዌስት የእውነቱን ለፕሬዝደንታዊ ምርጫ የመወዳደሩ ነገር ጥርጣሬን አላቸው።
በቻርልስተን ውስጥ ያካሄደው የምርጫ ቅስቀሳ ካኒዬ ዌስት የእውነት ለአሜሪካ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ለመወዳደሩ ማረጋገጫ ሊሆን አይችልም ተብሏል።
ካኒዬ ዌስት ትናንት ምሽት ባደረገው የምረጡኝ ዘመቻ ጭንቅላቱ ላይ “2020” የሚል ምልክት አድርጎ እና የጥይት መከላከያ ልብስ ለብሶ ታይቷል።
በአዳራሹ ለተሰበሰቡ ደጋፊዎቹም ያለ ማይክራፎን ወይም ድምጽ ማጉያ ንግግር ሲያደርግ አምሽቷል።
ስለ ጽንስ ማቋረጥ እየተናገረ ሳለ ማልቀስም ጀምሮ ነበር። ካኒዬ ዌስት ወላጆቼ ጽንስ ማቀወረጥ ሊፈጽሙብኝ ነበር ሲል በስሜት ሆኖ ተናግሯል።
ካኒዬ ዌስት እአአ 2007 በሞት ስለተለዩት ወላጅ እናቱም ስሜታዊ ሆኖ ብዙ ነገር ተናግሯል።
ካኒዬ ዌስት በዚህ ወር መጀሪያ ላይ ነበር በ2020 የአሜሪካ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ተወዳዳሪ እንደሚሆን ያስታወቀው። ይሁን እንጂ የምርጫው ተወዳዳሪ ለመሆን በበርካታ ግዛቶች በቂ የድጋፍ ፊርማ ማሰባሰብ ይኖርበታል።












