ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቀለበታዊው የፀሐይ ግርዶሽ በላልይበላ
ቀለበታዊ የፀሐይ ግርዶሽ በዛሬው ዕለት ዕሁድ ሰኔ 14/ 2012 ዓ.ም ጥዋት በኢትዮጵያ ታይቷል።
በብዙዎች ዘንድ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው ቀለበታዊ የፀሐይ ግርዶሽ ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ የምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ ይታያል።
በተለይም በላልይበላ አካባቢዎች ጨለምለም ብሎ የነበረ ሲሆን ቀለበታዊ የፀሐይ ግርዶሹም መታየቱን ቢቢሲ አረጋግጧል።
በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል ፀሐይ ከ80 በመቶ ተሸፍና በከፊል ግርዶሽነት የታየች ሲሆን በተወሰነው የደቡብ ኢትዮጵያ ክፍል ደግሞ ፀሐይ ከ60- 80 በመቶ ተሸፍና ግርዶሹ ታይቷል። ዋናው ግርዶሽ ግን ከምዕራብ ኢትዮጵያ አንስቶ እስከ ሰሜን ምስራቅ ድረስ የሚዘልቀው ነው።
ክስተቱም ወለጋ ጀምሮ፣ በከፊል ጎጃምንና ጎንደርን አቆራርጦ ነው ወደ ወሎ በመሻገር ላሊበላንም ያዳረሰ እንደሆነም የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አስታውቋል።
በእነዚህ ቦታዎች ፀሐይ እስከ 98 በመቶ ተሸፍና ቀለበታዊውን ግርዶሽም ማየት ተችሏል። ይህንን ቀለበታዊ ግርዶሽ ማየት ከቻሉ አካባቢዎች መካከልም ላሊበላን ጨምሮ ቆቦ፣ ኮረም፣ አላማጣ፣ በጊ፣ ሜቲ፣ እንጅባራ፣ ቡሬ፣ አገው ግምጃ ቤት፣ጋይንት፣ ንፋስ መውጫ፣ ግሽ አባይ የተወሰኑት ናቸው።
ግርዶሹ ከጥዋቱ 12፡45 ጀምሮ እስከ ስድስት ሰዓት ተኩል የቆየ ነበር ተብሏል።
ቀለበታዊ ግርዶሽ የሚከሰተው ጨረቃ በፀሐይና በምድር መካከል ስትሆን እንዲሁም ፀሐይ ሙሉ በሙሉ ተጋርዳ ብርሃን መስጠት ሳትችል ነው።
ጨረቃ በፀሐይና መሬት መካከል ስትሆን የሚፈጠረውንም ክስተት ለማየት ብዙዎችም ወደ ላልይበላ ተጉዘዋል።
እንዲህ አይነት ታሪካዊ ክስተት በድጋሚ የሚያጋጥመው ከ18 ዓመታት በኋላ ሲሆን ሙሉ የፀሐይ ግርዶሽ የሚኖረው ከ146 ዓመታት በኋላ እንደሆነ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከለሰሞኑ አስታውቋል።
ቀለበታዊ የፀሐይ ግርዶሽ ከኮንጎ ተነስቶ፣ ማዕከላ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን ኢትዮጵያንና ኤርትራን አዳርሶ ወደ መካከለኛው ምሥራቅም ይሻገራል።