ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኮሮናቫይረስ ጽኑ ህሙማንን ህይወት ይታደጋል የተባለውን መድኃኒት የዓለም ጤና ድርጅት ተቀበለው
በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ዴክሳሜታሶን በተባለው መድኃኒት ላይ የተደረገው ሙከራና ያስገኘውን ውጤት በበጎ እንደሚመለከተው የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ።
በሙከራው ይህ መድኃኒት በኮሮናቫይረስ በጽኑ ከታመሙ ሰዎች የአንድ ሦስተኛውን ሕይወት መታደግ እንደሚችል እና በወረርሽኙ ሰበብ ኦክስጂን በሚያስፈልጋቸው ሰዎች ላይ የሚያጋጥምን ሞት በአንድ አምስተኛ ሊቀንስ እንደሚችል ለድርጅቱ የቀረበው የመጀመሪያ ደረጃ ግኝት አመልክቷል።
ድርጅቱ እንዳለው የዴክሳሜታሶን ጠቀሜታ በኮቪድ-19 በጸና በታመሙ ሰዎች ላይ እንጂ ቀለል ያለ ህመም ባለቸው ላይ እንዳልሆነ አመልክቷል።
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድኃኖም እንዳሉት "ይህ ኦክስጂንና የመተንፈሻ መርጃ መሳሪያ ለሚያስፈልጋቸው የኮሮናቫይረስ ህሙማን ላይ የሚያጋጥምን ሞት የሚቀንስ የመጀመሪያው መድኃኒት ነው" ብለዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ ይህም ታላቅ ዜና መሆኑን ጠቅሰው የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥትንና ይህንን ህይወትን የሚታደግ የመጀመሪያ ግኝት ላይ በመሳተፍ አስተዋጽኦ ላበረከቱት ለኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ፣ ለሆስፒታሎችና ለህሙማን የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ዴክሳሜታሶን ከ1960ዎቹ (እአአ) ጀምሮ በተለያዩ ህመሞች ምክንያት የሚያጋጥሙ እብጠቶችን ለመቀነስና የተወሰኑ አይነት የካንስር ህመሞችን ለማከም ጥቅም ሲውል ቆይቷል።
በርካሽ ዋጋና በስፋት የሚገኘው ዴክሳሜታሶን በኮቪድ-19 በጽኑ የታመሙ ሰዎች ሕይወት አድን መሆኑን የዩናይትድ ኪንግደም ባለሙያዎች ገለፁ።
መድኃኒቱን በአነስተኛ መጠን በመስጠት ማከም ይህንን ገዳይ ቫይረስ በመዋጋት ረገድ ወሳኝ መሆኑን ባለሙያዎቹ ይናገራሉ።
ተመራማሪዎች የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እንደተከሰተ በዩናይትድ ኪንግደም መድኃኒቱ በስፋት ቢገኝ ኖሮ እስካሁን ድረስ የ5000 ሰዎችን ሕይወት ማዳን ይቻል ነበር ብለዋል።
ምክንያታቸው ደግሞ ርካሽ መሆኑ ሲሆን ከፍተኛ የኮቪድ-19 ሕሙማን ባሏቸው ደሃ አገራት ውስጥም ቢሆን በርካታ ጥቅም እንዳለው ያስረዳሉ።
ዴክሳሜታሶን ለጽኑ ሕሙማን በደም ስር የሚሰጥ ሲሆን፣ ሕመማቸው ላልፀናባቸው ደግሞ በክኒን መልክ እንዲወስዱት ይደረጋል ተብሏል።
መድኃኒቱ ከ1977 ጀምሮ በተለያየ መልኩ ተዘጋጅቶ አስፈላጊ ከተባሉ የዓለም ጤና ድርጅት የመድኃኒቶች ዝርዝር ውስጥ የገባ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ከባለቤትነት መብት ነጻ ከመሆኑ በተጨማሪ በብዙ አገራት ውስጥ በቀላሉ ይገኛል ተብለወል።
ተመራማሪዎች የመጀመሪያ ደረጃ ሙከራ ውጤታቸውን ለዓለም ጤና ድርጅት ያሳውቀው በቀጣይ ቀናትን ስለዴክሳሜታሶን ያለው ሙሉ መረጃ ተተንትኖ እንደሚቀርብ እየተጠበቀ ነው።
በቀጣይም ድርጅቱ ስለመድኃኒቱ ተጨማሪ መረጃዎችን እንደሚያቀርብና ስለመድኃኒቱ አጠቃቀም ያለው መመሪያ ላይ መሻሻል ያደርጋል ተብሏል።