በለንደን ሃውልት እንጠብቃለን በሚሉና በፖሊስ መካከል በተከሰተ ግጭት ከ100 በላይ ሰዎች ታሰሩ

የፎቶው ባለመብት, PA Media
ቅዳሜ ዕለት በለንደን በተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ ከ100 በላይ ሰዎች መታሰራቸውን የከተማዋ ፖሊስ አስታውቋል፡፡
በወቅቱ ተቃዋሚዎች በፖሊስ ላይ ጥቃት የፈጸሙ ሲሆን ከጥቃት አድራሾቹ አንዳንዶቹ የቀኝ አክራሪነት አቀንቃኞች ናቸው ተብሏል፡፡
ግጭቱ የተቀሰቀሰው በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የቸርችል ሃውልትን ለመጠበቅ ከተሰባሰቡ በኋላ ነው፡፡
በርካታ የቀኝ አክራሪ ቡድኖች የቀድሞውን የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዊንስተን ቸርችል ሃውልትን ከመገርሰስ ለማዳን ወደ ለንደን የመጡ ሲሆን አብዛኛዎቹም ነጭ ወንዶች እንደሆኑም ተነግሯል።
ግለሰሰቦቹ የዊንስተን ቸርችል ሃውልትን ከበው በመጠበቅ ላይ ነበሩ። እነዚህ ተቃዋሚዎች ከፖሊስ ጋር በፈጠሩት ግጭት ስድስት የሚሆኑ ፖሊሶች ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ዊንስተን ቸርችል በነጭ እንግሊዛውያን ዘንድ አገሪቱን ለሁለተኛ ዓለም ጦርነት ድል ያበቃ መሪ እንዲሁም ድንቅ መሪ፣ ፀሐፊና ተናጋሪ ቢሉትም ከነጭ ዘር ውጪ በነበረው ንቀት አወዛጋቢም ሆኗል።
በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር የዘር አከፋፈል መሰረት ከላይ የሚቀመጡት ነጭ ፕሮቴስታንቶች፣ በመቀጠል ነጭ ካቶሊኮች ከዚያም ከአፍሪካውያን በልጠው ህንዳውያን ናቸው። አፍሪካውያን የመጨረሻውን ቦታ ሲይዙም ከሰውም ያነሱ ናቸው ብሎ ያምን ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስተር ቦሪስ ጆንሰን ድርጊቱን "የዘረኝነት ልክ ያለፈ ቁጣ በመንገዳችን ላይ ቦታ የለውም" ብለዋል፡፡
ከሦስት ዓመታት በፊት በዌስትሚኒስተር ጥቃት በተገደለው በፒሲ ኬት ፓልመር መታሰቢያ ሃውልት ስር አንድ ግለሰብ ሽንቱን ሲሸና መታየቱን ተከትሎም ምርመራዎች እየተደረጉ ነው፡፡
የአገር ውስጥ ሚኒስትር ፕሪቲ ፓቴልም በመታሰቢያ ሃውልቱ ላይ የተፈጸመውን ድርጊት "በጣም አሳፋሪ" ሲሉ ኮንነውታል፡፡
የከተማዋ ፖሊስ ኮማንደር ባስ ጃቪድ በበኩላቸው፤ "አንድ ግለሰብ በመታሰቢያ ሃውልቱ ስር ሽንቱን ሲሸና የሚያሳይና በጣም አጸያፊ የሆነ ምስል በማህበራዊ ሚዲያዎች ሲዘዋወር ተመልክተናል፤ ምርመራ የጀመርነውም ወዲያውኑ ነው፡፡ ማስረጃዎቹን ከሰበሰብን በኋላ ተገቢውን እርምጃ እንወስዳለን" ብለዋል፡፡
ከሦስት ዓመታት በፊት ፒሲ ፓልመር በዌስትሚኒስተር ደጅ ላይ በካሊድ ማሱድ በተፈጸመ የሽብር ጥቃት ተጎድተው ሳለ የመጀመሪያ ሕክምና እርዳታ የሰጧቸው የፓርላማ አባል ቶቢያስ ኢልውድም፤ በመታሰቢያ ሃውልታቸው ላይ የተፈጸመው ድርጊት አጸያፊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
"ግለሰቡ ሲያደርግ የነበረውን ያውቀዋል፤ በመሆኑም ራሱን በማጋለጥ ይቅርታ ሊጠይቅ ይገባልም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል፡፡
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ
ቅዳሜ እለት በለንደንና በሌሎች የአገሪቷ ክፍሎች ሰላማዊ የሆኑ ጸረ -ዘረኝነት ተቃውሞዎችም ተካሂደዋል፡፡
ከሰሞኑም በዩናይትድ ኪንግደም መዲና በሚገኘው የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዊንስተን ቸርችል በተቃዋሚዎች ዘንድ ዘረኛ የሚል ጽሁፍ ተጽፎበት ታይቷል፡፡
የጥቁር አሜሪካዊውን ጆርጅ ፍሎይድ በነጭ ፖሊስ እጅ መሞቱን ተከትሎ የተቀጣጠለው ተቃውሞ በምዕራባዊን ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው አሳሾች እና ነገሥታት ሃውልቶች እንዲገረሰሱና ተመሳሳይ ድርጊቶች እንዲፈጸሙ አነሳስቷል፡፡
ምንም እንኳን እነዚህ ሰዎች ለምዕራባውያኑ ትልቅ ቢሆኑም በአፍሪካውያንም ሆነ በደቡቡ ዓለም ጭፍጨፋ፣ ዝርፊያና መደፈርን ሌሎች አሳፋሪ ታሪኮችን የፈፀሙ ናቸው።












