በአትላንታ ጥቁር አሜሪካዊው በፖሊስ መገደልን ተከትሎ የፖሊስ ኃላፊዋ ሥራቸውን ለቀቁ

በአትላንታ የተነሳው ተቃውሞ

የፎቶው ባለመብት, EPA

በአትላንታ በሚገኘው ዌንዲስ ሬስቶራንት በር ላይ መኪናው ውስጥ ተኝቶ የነበረው ጥቁር አሜሪካዊ በፖሊስ መገደልን ተከትሎ የአትላንታ ፖሊስ ኃላፊ ከሥራቸው ለቀዋል።

የ27 ዓመቱ ጥቁር አሜሪካዊ ራይሻርድ ብሩክስ በፖሊስ በተተኮሰበት ጥይት የተገደለው አርብ ዕለት መሆኑን ባለስልጣናቱ አስታውቀዋል።

የአትላንታ ከንቲባ ኬይሻ ላንስ ቦተምስ እንዳሳወቁት የፖሊስ ኃላፊዋ መልቀቂያቸውን በትናንትናው ዕለት ማስገባታቸውን ነው።

ግድያውንም ተከትሎ ሰልፈኞች ተቃውሟቸውን ለመግለፅ ወደ አደባባይ ወጥተዋል።

ቅዳሜ ምሽትም ኢንተርስቴት-75 የተባለው የከተማውን ትልቁን አውራ ጎዳና በተቃዋሚዎች ተዘግቷል። ራይሻርድ ብሩክስ የተገደለበት ዌንዲስ ሬስቶራንትም በተቃዋሚዎች በእሳት ጋይቷል።

በእሳት የጋየው ዌንዲስ ሬስቶራንት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በባለፉት ሦስት ሳምንታት በነጭ ፖሊስ የተገደለውን ጆርጅ ፍሎይድን ግድያን ተከትሎ ተቃውሞዎች የተቀጣጠሉ ሲሆን በአትላንታም የራይሻርድ ብሩክስ መገደል ተቃውሞው ወደ ከፍተኛ ደረጃ እንዲሻገር አድርጎታል።

ኤሪካ ሺልድስ በፖሊስ ኃላፊነት ለአራት ዓመታት እንዲሁም በተራ ፖሊስነትም ለሃያ ዓመታት ያህል ማገልገሏ ተገልጿል።

ከንቲባዋ አክለውም ከፖሊስ ኃላፊነቷ ብትነሳም በሌላ የሥራ ድርሻ እንደምትሳተፍ አሳውቀዋል። በተጨማሪም ራይሻርድ ብሩክስን የገደለው ፖሊስም ከሥራ እንዲባረር ከንቲባዋ ጠይቀዋል።

አርብ ዕለት ምን ተፈጠረ?

የጆርጂያ የምርመራ ቢሮ ከዌንዲስ ሬስቶራንት ያገኘውን እንዲሁም በዓይን እማኞች አማካኝነት የተቀረፁትን ቪዲዮዎች እየመረመረ ይገኛል።

ራይሻርድ ብሩክስ ከሬስቶራንቱ ውጭ መኪናው ውስጥ ተኝቶ የነበረ ሲሆን ከኋላውም ለነበረው መኪና መተላለፊያ ዘግቷልም በሚል ፖሊስ ጋር መደወሉ ተገልጿል።

ፖሊስ እንደሚለውም ራይሻርድ ብሩክስ መጠጥ ከሚፈቀደው በላይ ጠጥቶ እንደነበርና በቁጥጥር ስር ለማዋልም ሲሞክሩ እምቢተኝነቱን ኣሳይቷል።

በአትላንታ የሚገኝ ተቃዋሚ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምርመራ ቢሮው ከሬስቶራንቱ አገኘሁት ባለው ቪዲዮ ፖሊሶች ራይሻርድ ብሩክስን ሲያሯሩጡት እንደነበርና ብሩክስም የማደንዘዣ መሳያ (ቴዘር) በአንደኛው ፖሊስ ላይ ደግኗል ተብሏል።

"ፖሊሱ በጥቁር አሜሪካዊው ላይ ሽጉጥ እንደተኮሰበትም" ሪፖርቱ አትቷል።

በሌላ በኩል ከዓይን እማኝ የተገኘው ቪዲዮ ዌንዲስ ሬስቶራንት ውጭ ላይ ሁለት ፖሊሶች ጥቁር አሜሪካዊውን ከላይ ተጭነውት እንደነበርና ከእነሱም ነፃ ለመውጣት ሲታገል ነበር።

ድንገትም ከአንደኛው ፖሊስ 'የማደንዘዣ መሳሪያ (ቴዘሩን) ቀምቶ መሮጥ ጀመረ። ሌላኛው ፖሊስ ጥቁር አሜሪካዊውንም ሆነ ሁለቱን ፖሊሶች በማደንዘዣ መሳሪያው ካደነዘዛቸው በኋላ ቪዲዮው ላይ መታየት ያቆማል።

ከዚያም የጥይት ድምፅ የሚሰማ ሲሆን ብሩክስም መሬት ላይ ሲወድቅ ይታያል።

ከዚያም ወደ ሆስፒታል ቢወሰድም ህይወቱ ሊተርፍ አልቻለም። አንደኛው ፖሊስም ጉዳት ደርሶበት ህክምና አግኝቷል ተብሏል።

በአትላንታ የተነሳው ተቃውሞ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የፎልተን ግዛት ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በበኩሉ የተለየ ምርመራ እያካሄደ እንደሆነ በመግለጫው ጠቁሟል።

የራይሻርድ ብሩክስ የቤተሰብ ጠበቆች በበኩላቸው "ፖሊሶቹ ሽጉጥ ለመተኮሳቸው ምንም አይነት አሳማኝ ምክንያት የላቸውም፤ ራይሻርድ የወሰደው ማደንዘዣ መሳሪያ ገዳይ አይደለም" ብለዋል።

"አንድ ሰው ሽጉጥ እስካልደገነብህ ድረስ መተኮስ አትችልም" በማለት ጠበቃው ክሪስ ስቲዋርት ገልፀዋል።

ራይሻርድ ብሩክስ የስምንት ዓመት ልጁን ልደት ለማክበር ወደ ስኬቲንግ ቦታ ለመውሰድም ቅዳሜ እለት አቅዶ እንደነበር ጠበቃው ገልጸዋል።

የራይሻርድ ብሩክስን በሽጉጥ መገደል ጨምሮ በዚህ ዓመት ብቻ 48 ግለሰቦች በፖሊስ ጥይት ከመመታታቸው ጋር ተያይዞ የጆርጂያ ቢሮ ምርመራ መክፈቱን ኤቢሲ ዘግቧል። ከእነዚህም ውስጥ አስራ አምስቱ ሞተዋል።

በርካታ ሰዎች በዌንዲስ ሬስቶራንት ውጭ ተቃውሟቸውን አርብ እለት የገለፁ ሲሆን ይሄም ቅዳሜ ቀጥሎ ወደ ከተማዋ ማዕከል መዛመቱንም ኒው ዮርክ ታይምስ ዘግቧል።

በርካቶች የራይሻርድ ብሩክስን ስም ይዘው እንዲሁም ብላክ ላይቭስ ማተር መልእክቶችንና መፈክሮች ሲያሰሙ ነበር።

የአትላንታ ሰዎች በሚኒያፖሊስ በነጭ ፖሊስ የተገደለው ጆርጅ ፍሎይድ ግድያ ሲቃወሙ ሰንብተዋል። በጆርጅ ፍሎይድ ግድያም የተወነጀለው ፖሊስ በሁለተኛ ደረጃ የሰው ግድያ ወንጀል ተከሷል።