ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአዲስ አበባ የአንድ መንደር ነዋሪዎች እራሳቸውን ለይተው ተቀመጡ
የጤና ጥበቃ ሚንስቴር እና የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በጋራ በሚያወጡት ዕለታዊ መግለጫ ላይ በኢትዮጵያ ኮሮናቫይረስ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ከ700 በላይ ሆኗል።
በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ የኮሮናቫይረስ ከተገኘባቸው ሰዎች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የሚገኙት በመዲናዋ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ እንደሆነ እስካሁን የወጡት አሃዞች አመልክተዋል።
በከተማዋ ውስጥ ደግሞ በዋነኛነት የልደታና የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተሞች ውስጥ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ እንደሆነ ተነግሯል። በልደታ ክፍለ ከተማ እስካሁን 122 ሰዎች በበሽታው እንደተያዙና በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ደግሞ 69 ሰዎች ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ተገልጿል።
ከአንድ ወር በፊት የበሽታውን መስፋፋት በተመለከተ የሚወጡት መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች መካከል ሁሉም በሚባል ደረጃ የውጪ አገራት የጉዞ ያላቸው ወይም ከእነሱ ጋር ንክክኪ የነበራቸው እንደሆኑ ተገልጿል።
ከባለፈው ሳምንት ወዲህ የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ግን በበሽታው ተይዘው የሚገኙ አብዛኞቹ ሰዎች የውጪ ጉዞ ታሪክ ወይም ከውጪ አገራት ከመጣ ሰው ጋር ግንኙነት የሌላቸው ናቸው።
ይህ ደግሞ ወረርሽኙ በማኅበረሰቡ ውስጥ ገብቶ ውስጥ ለውስጥ እየተሰራጨ እንደሚገኝ የሚያመለክት እንደሆነ የሕብረተሰብ ጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ። ስለዚህም በተለይ በስፋት ምርመራ በማድረግ በርካታ ህሙማን የተገኙባቸውን አካባቢዎች በመለየት ጥብቅ የመቆጣጠሪያ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ይመክራሉ።
ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ የጤና ጥበቃ ሚንስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ፤ የቫይረሱ ስርጭት በስፋት በታየባቸው የአዲስ አበባ ክፍለ ከተሞች የእንቅስቃሴ እገዳ ሊደረግ እንደሚችል መናጋራቸውም ይታወሳል።
በእነዚህ የአዲስ አበባ ክፍሎች በተለይ ደግሞ የበሽታው ክስተት በታየባቸው አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች ከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንደሆኑ ለቢቢሲ ገልጸዋል። አንዳንዶችም በእራሳቸው ተነሳሽነት የበሽታውን መዛመት ለመግታት የሚያስችሉ እርምጃዎችና ቁጥጥር በአካባቢያቸው እያደረጉ ይገኛሉ።
ከእነዚህም መካከል በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ቀጠና አምስት መንደር ሦስት ውስጥ የሚኖሩ 74 አባወራዎች የሚኖሩበት መንደር ነው።
ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ ሕይወታቸው ያለፈው የ78 ዓመት ሴት ከዚህች መንደር ነዋሪዎች ጋር ንክኪ ስለነበራቸው የአካባቢው ወጣቶች ነዋሪውን በማስተባበር እራሳቸውን ለይተዋል።
የመንደሪቱ ነዋሪና አስተባበሪ የሆነው ቢንያም አሸናፊ "መንግሥት አስገድዶን ሳይሆን በበጎ ፈቃዳችን ነው እራሳችንን የለየነው። ሕብረተሰቡ ለኮሮናቫይረስ ምርመራ ናሙና ስለሰጠ ውጤታችን እስከሚታወቅ ድረስ ነው የመንደሪቱን እንቅስቃሴ ያቆምነው" ይላል።
"እና እያደረግን ያለነው 74 አባወራዎች የሚኖሩበት ቅያስ መንገድ በመዝጋት የምርመራው ውጤት እስከሚታወቅ ድረስ ለሁለት ሳምንታት ከሰዎች ጋር ያለንን ንክኪ ማቋረጥ ነው።‘’
እራሳቸውን ከለዩ አንድ ሳምንት እንደሆናቸው የሚናገረው ቢንያም ራስን ማግለሉ በበጎ ፈቃድ ላይ የተመሰረት በመሆኑ መግባትና መውጣት ሙሉ በሙሉ አልተከለከለም ይላል።
በአካባቢው በየቀኑ ከሚሰሩት ሥራ የዕለት ጉርሳቸውን ለማግኘት መንቀሳቀስ ግድ የሚላቸው ሰዎች መኖራቸውን የጠቀሰው ቢኒያም "እነሱን ማስገደድ አልቻልንም። በእጃችን ላይ ለእነሱ የሚበላና የሚጠጣ ለማሟላት ስለማንቸል ምንም ማድረግ አልቻልንም" በማለት ያለባቸውን ችግር ገልጿል።
ነገር ግን ይላል ቢንያም አብዛኛው "ንክኪ ሊኖረኝ ይችላል" ብሎ የሚያስበው ሰው እራሱን ለይቶ ለተከታታይ ቀናት በቤቱ ተቀምጧል።
የበሽታው ስጋት
ባለፉት ሳምንታት በአካባቢው በነበሩ ለቅሶና እድርን በመሳሰሉ ማኅበራዊ ክንውኖች ወቅት ብዙ ሰዎች ንክኪ አድርገዋል ብለው የሚያምኑት ነዋሪዎች ስጋት አላቸው። በተጨማሪም የአካባቢው ቤቶች አሰራርና የሰዎች አኗኗር በጣም በተጠጋጋ ሁኔታ ስለሆነ ለዚህ ውሳኔ ምክንያት ሆኗል።
"በዚህ ምክንያት ብዙ ሰው እራሱን አግልሏል፤ እኔም እራሴን አግልዬ ነው የምገኘው" ይላል ቢኒያም።
አስተባባሪዎቹ ከአንዳንድ ግብረሰናይ ግለሰቦችና ከወረዳው ጋር በመተባበር ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎችን በቤታቸው እራሳቸውን ለይተው እንዲቀመጡ የሚያደርጉት ሥራ የበሽታውን መስፋፋት ለመቆጣጠርና ሌሎችን ለመጠበቅ ጠቃሚ እርምጃ መሆኑን ቢንያምና የአካባቢው ነዋሪዎች ያምናሉ።
ነዋሪዎቹ ይህንን እርምጃ የወሰዱት ከአካባቢው መስተዳደር ጋር በመነጋገር እንደሆነ አመልክተው ማንም እንዳላስገደዳቸው አስተባባሪው ቢኒያም ተናግሯል።
ሰኞ ዕለት ቢቢሲ ያነጋገራቸው አንዳንድ የአይን እማኞችና የመገናኛ ብዙሃን በአካባቢው ፖሊስ ተሰማርቶ ቁጥጥር እያደረገ እንደሆነና አስገዳጅ የእንቅስቃሴ ገደብ መጣሉን ቢገልጹም፤ ቢንያም ግን "ፖሊሶቹ እንቅስቃሴ ለመከልከል ሳይሆን ለተለመደ ሥራቸው ነው የተሰማሩት" ሲል ለቢቢሲ ገልጿል።
የዚህ የአካባቢው ነዋሪ በአሁኑ ጊዜ ከተለመደው እንቅስቃሴ ተቆጥቦ ያለ ከመሆኑ በተጨማሪ፤ ሁለት ወይም ሦስት የሚሆኑ ቤቶች ውስጥ የሚኖሩ ሙሉ የቤተሰብ አባላት በበሽታው ተጠርጥረው ወይም መያዛቸው ተረጋግጦ ለይቶ ማቆያ ውስጥ የገቡበት ሁኔታ እንዳለም ተነግሯል።
ቢኒያም እንደጠቀሰው እሱና ሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎች ይህንን እርምጃ እየተቆጣጠሩ ያሉት በበጎ ፈቃደኝነት መሆኑን ገልጾ፤ ወደ ለይቶ ማቆያ የገቡትን ሰዎች ቤት ለመጠበቅ የፖሊስ እገዛ ተደርጎላቸዋል።
"ከወረዳው ጋር በመነጋገር የፖሊስ ድጋፍ እንዲደረግ የጠየቅነው እንጂ ፖሊሶቹ መውጣት መግባት እንዲከለክሉ አይደለም የመጡት።" ይላል።
የሚያስፈልግ ድጋፍ
እራሳቸውን ለይተው ለተቀመጡት በጎ ፈቃደኛ ነዋሪዎች ደግሞ ለሁሉም በቂ ነው ባይባልም እንደ ዘይት፣ ዱቄትና ፓስታን የመሳሰሉ የምግብ አይነቶች እየቀረቡ እንደሆነ ቢንያም ነግሮናል።
በተጨማሪም በተለያዩ ሥራዎች ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ሰዎች ከሚሰሩበት መስሪያ ቤት ግብአቶችን ሰብስበው የሚያመጡ በጎ ፈቃደኞችም እንዳሉ ቢኒያም ለቢቢሲ ገልጿል።
ለምሳሌም የሴቶች ንጽህና መጠበቂያ፣ የህጻናት ወተት፣ ዳይፐርና መሰል መገልገያዎች በአካባቢው ሰዎችና ሌሎች በጎ ፈቃደኞች እየቀረቡላቸው ነው።
ቢንያም እንደነገረን እራስን የማግለሉ እርምጃ በዋናነት ቫይረሱ ቢገኝባቸው ወደ ሌሎች ሰዎችና አካባቢዎች ላለማስተላለፍ በእራስ ውሳኔና በጎ ፈቃድ የተወሰደ እርምጃ ነው።
"የምንኖርበት አካባቢ በጣም የተጨናነቀ ነው፤ ሌላው ቀርቶ ኩሽና እና ሽንት ቤት ብዙ ሰዎች በጋራ ይጠቀሟቸዋል። በትንሽ ጠባብ ቤት ውስጥም እስከ አምስት የሚደርሱ ሰዎች አብረው ይኖራሉ። በዚህ ሁኔታ ከቫይረሱ ማምለጥ ከባድ ነው።"
"ስለዚህ በተቻለ መጠን ብዙ ሰው ናሙና እንዲሰጥ ተደርጓል። ዋናው ስጋታችን መንደራችን ውስጥ ብዙ ሰዎች ቫይረሱ ቢገኝባቸው ወደ ሌሎች እንዳናስተላልፍ ነው፤ ለዚህም ነው እራሳችንን ማግለል የመረጥነው" ሲል የአካባቢው ኅብረተሰብ ለሌሎች ሲል ይህንን እርምጃ በእራሱ ላይ ያለማንም ጫና መውሰዱን ቢኒያም አሸናፊ ይናገራል።