"ፖሊስ በጓደኛዬ ላይ እንዲተኩስ የሚያደርግ አንድም ምክንያት አልነበረም" የሟች ሽሻይ ጓደኛ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በትግራይ ክልል፤ በመቀለ ከተማ 05 ቀበሌ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ተሰብስበው የነበሩ ወጣቶችን ለመበተን በተደረገው ጥረት ግጭት ተከስቶ አንድ ወጣት በፖሊስ አባል መደገሉን የከተማው ፖሊስ ጽህፈት ቤት ለቢቢሲ ገለጸ።
ፖሊስ እንዳለው ከሆነ የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት መጠጥ ቤቶች ዝግ መሆናቸውን ተከትሎ ወጣቶች 05 ቀበሌ በተባለው አካባቢ በአንድ ላይ ተሰባሰበው እየጠጡ ነው የሚል መረጃ እንደደረሰው አስታውቋል።
በጥቆማው መሠረት ፖሊስ ወደተባለበት ሥፍራ ተሰማርቶ ወጣቶቹ እንዲበተኑ ለማድረግ ሲጥር፤ በተፈጠረ ግጭት የአንድ ሰው ህይወት አልፏል ብሏል። ከዚህ በተጨማሪም በሁለት ወጣቶች ላይ ጉዳት መድረሱ ተነግሯል።
በጠፋው ህይወት የተጠረጠረው ፖሊስም በቁጥጥር ሥር መዋሉን የከተማው ፖሊስ ለቢቢሲ አስታውቋል።
ፖሊስ በሟች ሽሻይ ኪሮስ ላይ እንዲተኩስ የሚያደርግ አንድም ምክንያት እንዳልነበረ ጓደኛው ለቢቢሲ ተናግሯል።
«በሰፈራችን ቁጭ ብለን ስንጫወት ነበር። ከዚያ ሁለት ፖሊሶች መጡ ሁለተኛው ፖሊስ ብረት ይዞ ነበር። ምን እያደረጋቹ ነው? አለን እሁድ ስለሆነ እየተጫወትን ነው አልነው። ከዛ ወደ ኮምዩኒቲ ፖሊስ እንሂድ አለን። እኛም እዚሁ አናግረን አልነው። ከዛ ሁለተኛው ፖሊስ ምንድነው ብሎ ጥይቱን ተቀበለው እና ማቹ ጓደኛችን ምን ሆነህ ነው ሲለው አንተማ አቃጥለሃለው በማለት ተኮሰበት።»
የ23 አመቱ ሽሻይ ከልጅነቱ ጀምሮ ብረታ ብረት እየሠራ ቤተሰቦቹን ያስተዳድር እንደነበር ጓደኛው ይናገራል።
የወጣቱ የቀብር ስነ ስርአት ዛሬ ጠዋት በመቐለ ከተማ በገብረመንፈስቅዱስ ቤተክርስትያን ተፈፅሟል። የአካባቢው ወጣቶች ከቀብር በኋላ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ተዘጋጅተው እንደነበር ነገር ግን በኮሮናቫይረስ ምክንያት ሀሳባቸውን ቀይረው ለአካባቢው አስተዳደር ሁኔታውን እንዳሳወቁ ይናገራሉ።

ይህንን ግድያ የፈፀመው ፖሊስ ከቀበሌ 05 ዓይደር ወደሚባል አካባቢ በማምለጥ በአካባቢው በአንድ ህንፃ ቢደበቅም በዚህ ድርጊት የተቆጣ ህዝብ ህንፃውን ከቦት ነበር። ሆኖም የፖሊስ ኃላፊዎች እና ልዩ ሃይል ሰራዊት አካባቢውን ተቆጣጥረውታል።
የመቀለ ከተማ የወንጀል መከላከያ እና ማጣርያ ፅህፈት ቤት ኮማንደር አንድነት ለገሰ፤ ግድያውን የፈፀመው ፖሊስ በቁጥጥር ስር እንደዋለ ተናግረዋል። ከዚያ በኋላ በድርጊቱ የተበሳጩ ወጣቶች ወደ ኮሚዩኒቲ ፖሊስ ፅህፈት ቤት ቀጠና ራህዋ በመሄድ ከፀጥታ ሃይሎች ጋር ተጋጭተዋል።
ይህንን ተከትሎም ሁለት ወጣቶች ከፀጥታ አካላት በተተኮሶባቸው ጥይት ጉዳት ደርሶባቸዋል። የተጎዱት ወጣቶች፡ በአሁኑ ሰአት በመቀለ ከተማ በሚገኘው ዓይደር ከፍተኛ ሆስፒታል ሕክምና እያገኙ ነው። አንደኛው ወጣት እጁ ላይ የተመታ ሲሆን ሁለተኛው ወጣት ግን ጎኑን ስለተመታ ቀዶ ህክምና ተደርጎለት በጽኑ ህሙማን ማቆያ እንደሚገኝ ከሆስፒታሉ ህዝብ ግንኙነት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማስፈጸም የሚንቀሳቀሱ ፖሊሶች በክልሉ ግድያ ሲፈጽሙ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም።
ቀደም ሲልም በመጋቢት ወር፤ በትግራይ ናዕዴር ዓዴት በሚባለው ወረዳ አንድ ወጣት በጸጥታ ኃይል አባል መገደሉ ይታወሳል።
ሓጎስ ንጉሥ የተባለ ይህ ወጣት የተገደለው በተመሳሳይ ፖሊስ መጠጥ ቤት ውስጥ ተሰባስበው የነበሩ ሰዎችን ለመበተን ሲሞክር በተነሳ አለመግባባት ነበር።
በመላዋ አገሪቱ የኮሮናቫይረስን መስፋፋት ለመከላከል ከታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቀደም ብሎ የትግራይ ክልል ውስጥ የሰዎችን በአንድ ላይ መሰባሰብን የማስቀረት ክልከላ ጨምሮ የተለያዩ እገዳዎች ተጥለው ነበር።














