"ምዕራባውያን ለአፍሪካ ሃገር በቀል መድኃኒቶች ንቀት አለባቸው" ሲሉ የማዳጋስካሩ ፕሬዚዳንት ተቹ

ከሰሞኑ የማዳጋስካሩ ፕሬዚዳንት አንድሪ ራጆይሊና ለኮሮናቫይረስ ፈውስ ከተለያዩ አገር በቀል ዕፅዋት አግኝተናል ማለታቸውን ተከትሎ፤ ያልተፈተነ መድኃኒት ነው እንዲሁም በተለያዩ ሙከራዎች አላለፈም የሚሉ ትችቶች እየተሰሙ ነው።

ባለፈው ሳምንት የአለም ጤና ድርጅት ያልተፈተነ መድኃኒቶችን አትውሰዱ ብሎ ማስጠንቀቁንም ተከትሎ የማዳጋስካሩ ፕሬዚዳንት በሁኔታው ደስተኛ አልሆኑም።

ድርጅቱ ሃገር በቀል መድሃኒቶችን በሚጠቀሙበት ወቅት ተገቢ የሆኑ ሙከራዎችን ማለፋቸውን መረጋገጥ አለባቸው ብሏል።

የአለም ጤና ድርጅትም ሆነ የምዕራቡ አለም ሃገር በቀል የኮሮናቫይረስ መድሃኒትን የሚተቹት "ለአፍሪካ ሃገር በቀል መድሃኒት ንቀት ስላላቸውና የበላይ ነን ብለው ስለሚያስቡ ነው" በማለት ፕሬዚዳንቱ ትችታቸውን ለፈረንሳዩ ሚዲያ ፍራንስ 24 ተናግረዋል።

"መድኃኒቱን ያገኘቸው ማዳጋስካር ባትሆንና አንዷ አውሮፓዊ ሃገር ብትሆን በፈዋሽነቱ ላይ ጥርጣሬ ወይም ጥያቄ የሚነሳ ይመስላችኋል? በጭራሽ አይመስለኝም" ብለዋል

ፕሬዚዳንቱ ይህንን ይበሉ እንጂ መድኃኒቱ ፈዋሽ ስለመሆኑ በቂ መረጃ የለም ተብሏል። የአፍሪካ ህብረት መድኃኒቱ "ደህንነቱ የተጠበቀ መሆኑና አዳኝነቱን" በተመለከተ ሳይንሳዊ ድጋፎችን እንዲቀርቡለት ጠይቋል።

ይሁን እንጂ ጊኒ ቢሳው፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ታንዛንያና ላይቤሪያ ከዕፅዋት የተቀመመውን መድኃኒት ወደ ሃገራቸው እንዲመጣ አዘዋል፤ የተለያዩ የአፍሪካ ሃገራት መድሃኒቱን ወደ ሃገራቸው በማስገባት ላይ ይገኛሉ። ናይጄሪያም መድኃኒቱን እንደምትፈልግ አስታውቃለች።

የናይጄሪያ የኮሮናቫይረስ መቆጣጠሪያ ግብረ ኃይል እንዳስታወቀው ፕሬዚዳንት ሙሃማዱ ቡሃሪ መድኃኒቱ ወደ ናይጄሪያ እንዲገባ ፈቃድ ሰጥተዋል ብሏል። ሆኖም መድኃኒቱ ለኮሮና ህሙማን ከመሰጠቱ በፊት የማረጋገጫ ሂደቶች እንደሚከናወኑ አስታውቀዋል።

መድኃኒቱ የተሰራው የወባ በሽታንና ለሌሎችም በሽታዎች መድኃኒት ከሆነው የአሪቲ ቅጠል (አርቲሚዥያ)ና ሌሎችም ዕፅዋት መሆኑ ተነግሯል።

ከተለያዩ ዕፅዋት የተቀመመው መድኃኒት በባለፉት ሶስት ሳምንታት በሃያ ሰዎች ላይ ሙከራ መደረጉን የፕሬዚዳንቱ አማካሪ ለቢቢሲ ተናግረዋል። ይህም የአለም አቀፉ ጤና ድርጅት ካወጣው መመሪያ ጋር ይጣረሳል ተብሎም እየተተቸ ነው።

ከዚህም በተጨማሪ ሰዎች የቫይረሱን መዛመት ለመቆጣጠር የሚያደርጓቸውን ጥንቃቄዎች ችላ በማለት ራሳቸውን ሊያጋልጡ ይችላሉ እንዲሁም "ሃሰተኛ ተስፋን" ይሰጣል እየተባለ ነው።

ከሰሞኑም በአፍሪካ የአገር በቀል መድኃኒቶች ላይ ሰባ ባለሙያዎችን ያሳተፈ አንድ ስብሰባ የተደረገ ሲሆን፤ ባለሙያዎቹም የአገር በቀል መድኃኒቶች በተለያየ ሙከራ ሊያልፉ እንደሚገባ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን የአለም አቀፉ ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቅርንጫፍ በትዊተር ገፁ አስፍሯል።