7 ፓርቲዎች አሁን ላይ ላለው ችግር ምላሽ የሚሆነው 'ፖለቲካዊ መፍትሄ ነው' አሉ

ምርጫ

የፎቶው ባለመብት, ZACHARIAS ABUBEKER

7 ፖለቲካ ፓርቲዎች አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግሥት "ከመስከረም 30 በኋላ አገርን ማስተዳደር የሚያስችል ሕጋዊ መሰረት ሊኖረው አይችልም" በማለት አሁን ላለው ችግር ምላሽ የሚሰጠው ፖለቲካዊ መፍትሄ ነው ብለዋል።

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በነሐሴ ወር ለማካሄድ ታቅዶ የነበረውን ምርጫ ማስፈጸም አስቸጋሪ በመሆኑ መንግሥት የምርጫ ጊዜን በማራዘም ምርጫውን ማካሄድ ያስችላሉ ያላቸውን አራት አማራጮች ማቅረቡ ይታወሳል።

እነዚህም አማራጮች የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን መበተን፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ፣ ሕገ-መንግሥትን ማሻሻል እና የሕገ-መንግሥት ትርጓሜ መጠየቅ የሚሉ ናቸው።

7ቱ ፓርቲዎች፤ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር፣ የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር፣ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ፣ የአገው ብሔራዊ ሸንጎ፣ የሞቻ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ አረና ትግራይ ለሉዓላዊነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲ እንዲሁም ከፋ አረንጓዴ ፓርቲ ''መንግሥት ያቀረባቸውን አማራጮች ገምግመን የራሳችንን አቋም ይዘናል" ብለዋል።

7ቱ ፓርቲዎች ምን አሉ?

ከላይ የተጠቀሱት 7 ፖለቲካ ፓርቲዎች አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግሥት "ከመስከረም 30 በኋላ አገርን ማስተዳደር የሚያስችል ሕጋዊ መሰረት ሊኖረው አይችልም" ብለዋል።

መንግሥት ያቀረባቸው 4 አማራጮች "የመንግሥትን የሥራ ዘመን ለማራዘም የሚያስችል ሕገ-መንግሥታዊ መከራከሪያ ማቅረብም አይችሉም' ብለዋል።

ፓርቲዎቹ ባወጡት መግለጫ፤ "መፍትሔው የኮሮናቫይረስ አልፎ (ተወግዶ) ምርጫ እስክናካሂድ ድረስ የሚፈጠረውን የመንግስት የስልጣን ክፍተት ለመሙላት የሚረዳው ሀገራዊ የፖለቲካ ስምምነት ላይ መድረስ ብቻ ነው" ብለዋል።

ፓርቲዎቹ ለዚህ ችግር ምላሽ የሚሆነው "የፖለቲካ መፍትሄ" እንደሆነ የጠቆሙ ሲሆን፤ መፍትሄ ያሉትን በዝርዝር የሚገልጽ ሰነድ ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ለማቅረብም ዝግጅታችንን አጠናቀናል ብለዋል።

"ከዚህ ውጪ የሚወሰድ ማንኛውም እርምጃ ፖለቲካዊ፣ ሕጋዊና እና ሕዝባዊ ተቀባይነት ስለሌለው አገሪቱን ወደ ከፋ የፖለቲካ ቀውስና ብጥብጥ የሚወስድ ነው የሚል ስጋት አለን" በማለት ስጋታቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ቅቡልነት ያለው ስምምነት ላይ ለመድረስ፤ ውይይቱ እና ድርድሩ በገለልተኛ አካል እየተመራ በ2012 ምርጫ ለመሳተፍ የተመዝገቡ ፓርቲዎች ብቻ መሳተፍ እንዳለባቸው እና በድርድሩ የሚደረሰው ስምምነት በሁሉም ወገን ተፈጻሚነት የሚኖረው መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።