ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ ፕሬዝዳንት ትራምፕ የኮሮናቫይረስ ከቻይና ቤተ ሙከራ ስለመውጣቱ መረጃ አለኝ አሉ
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኮሮናቫይረስ ከቻይና ቤተ ሙከራ መውጣቱን የሚያመለክት ማስረጃ መመልከታቸውን በመግለጽ የአገራቸው የደኅንነት ተቋማት ከሚሉት ጋር እየተቃረኑ ነው።
ቀደም ሲል የአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት መስሪያ ቤት ዳይሬክትር ጽህፈት ቤት የወረርሽኙ ቫይረስ ከወዴት እንደመጣ ገና ምርመራ እያደረገ መሆኑን ገልጾ ነበር።
ነገር ግን ጽህፈት ቤቱ ይህ ኮቪድ-19 የተባለው ቫይረስ "ሰው ሰራሽ ወይም በቤተሙከራ ውስጥ የተፈጠረ" እንዳልሆነ እንደደረሰበት አመልክቷል።
ቻይና ይህንን የቫይረሱን በእሷ ቤተ ሙከራ ውስጥ መፈጠር የሚያመለክተውን ውንጀላ ውድቅ አድርጋ አሜሪካ በሽታውን በተመለከተ የወሰደችውን እርምጃ ተችታለች።
ወረርሽኙ ከሦስት ወራት በፊት ቻይና ውስጥ ከተቀሰቀሰ በኋላ ዓለምን በማዳረስ እስካሁን 230 ሺህ ሰዎችን የገደለ ሲሆን ከዚህ ውስጥም 63 ሺህዎቹ አሜሪካ ውስጥ የሞቱ ናቸው።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከቻይናዋ ዉሃን ከተማ ተነስቶ ከተዛመተ በኋላ እስካሁን ቢያንስ 3.2 ሚሊዮን ሰዎችን የያዘ ሲሆን አንድ ሚሊዮኖቹ ደግሞ አሜሪካዊያን ናቸው።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ትናንት ሐሙስ በዋይት ሐውስ ውስጥ በነበራቸው መግለጫ ላይ አንድ ጋዜጠኛ፤ ቫይረሱ ዉሃን ውስጥ ከሚገኘው በቫይረስ ላይ ምርምር ከሚያደርገው ተቋም ስለመውጣቱ በሙሉ ልብ እንዲናገሩ የሚያደርግ መረጃ እንዳላቸው ጠይቋቸው ነበረ።
ፕሬዝዳንቱ በምላሻቸውም "አዎ አለኝ" ሲሉ ያለምንም ማብራሪያ ስለቫይረሱ አመጣጥ የሚያመለክት መረጃው እንዳላቸው ተናግረዋል።
አክለውም "የዓለም ጤና ድርጅት በእራሱ ማፈር አለበት፤ እንደ ቻይና የሕዝብ ግንኙነት ተቋም ሆኖ ነው ሲሰራ የነበረው" ሲሉ አሁንም የክስ ጣታቸውን ድርጅቱ ላይ ቀስረዋል።
በሰነዘሩት አስተያየት ላይ የበለጠ ማብራሪያ እንዲሰጡ ኋላ ላይ የተጠየቁት ትራምፕ "በዚህ ላይ ማብራሪያ መስጠት አልችልም። ስለዚህ ጉዳይ እንድነግራችሁ አልተፈቀደልኝም" ሲሉ አድበስብሰውት አልፈዋል።
ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ትናንት ባወጣው ዘገባ ላይ እንዳመለከተው የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣናት የአገሪቱ የደኅንነት ተቋማት ቫይረሱ ከቻይናዋ ዉሃን ቤተ ሙከራ መውጣት አለመውጣቱን እንዲመረምሩ ጥያቄ አቅርበዋል።
በተጨማሪም አንድ ስማቸው ያልተጠቀሰ ባለስልጣን የደኅንነት ተቋማቱ ቻይናና የዓለም ጤና ድርጅት ገና በሽታው እንደተቀሰቀሰ ቫይረሱን የሚመለከት መረጃን ደብቀው እንደሆነ እንዲያጣሩ ቀደም ሲል መታዘዛቸውን ገልጸዋል።