ታዋቂው ሳኡዲ አረቢያዊው መብት ተሟጋች በእስር ቤት ሳሉ 'ህይወታቸው አለፈ'

እአአ ከ2013 ጀምሮ በእስር ላይ የነበሩት የሳኡዲ አረቢያ ታዋቂ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች በእስር ቤት መሞታቸውን አክቲቪስቶች ተናገሩ።

ዶክትር አብዱላህ አል-ሃሚድ የሳኡዲ ሲቪል እና ፖለቲካ መብቶች ማኅበር መስራች የነበሩ ሲሆን በስትሮክ ተመተው በህይወት እና ሞት መካከል መቆየታቸው ተነግሯል።

የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎች ዶ/ር አብዱላህ አል-ሃሚድ ከእስር እንዲለቀቁ በተደጋጋሚ ጫና ሲያሳድሩ ቆይተዋል።

በሰብዓዊ መብት አያያዝ የሚተቸው የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት በአክቲቪስቱ የሞት ሪፖርት ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።

የ69 ዓመት አዛውንት ከሆኑት ዶ/ር አብዱላህ አል-ሃሚድ ጋር ሞሐመድ አል-ቃሃታኒ የተባሉ አክቲቪስትም ለእስር ተዳርገው ነበር። ሁለቱ አክቲቪስቶች "አለመረጋጋትን በመፍጠር" ጥፋተኛ ተብለው እያንዳንዳቸው የ10 እና 11 ዓመት እስር ተበይኖባቸው ነበር።

የሳኡዲ አረቢያ የመብት ተሟጋቾች ዶ/ር አል-ሃሚድ በቂ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ አልተደረገም ሲሉ የሳኡዲ አረቢያን መንግሥት ይተቻሉ።

ዶ/ር አል-ሃሚድ ካለፉት ሁለት ሳምንታት ወዲህ ጤናቸው መቃወሱ ተነግሯል።

መቀመጫቸውን ዩናይትድ ኪንግደም የደረጉት እና የሳኡዲ መንግሥት ተቺ የሆኑት መምህርት ማዳዊ አል-ራሺድ፤ ዶ/ር አል-ሃሚድን "የሰብዓዊ መብት ትግል ምልክት" ሲሉ ይገልጿቸዋል።

የሳኡዲ የሲቪል እና ፖለቲካል መብቶች ማኅበር መስራቾቹ ክስ ከተመሰረተባቸው በኋላ እንዲዘጋ ተደርጓል።