ኮሮናቫይረስ፡ ልናውቃቸው የሚገቡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዝርዝር ይዘቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መስፋፋትን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ በተወካዮች ምክር ቤት ጸድቆ ለአምስት ወራት በመላዋ አገሪቱ ተግባራዊ እንዲሆን የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዝርዝር ይዘት ወጥቷል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት የወረርሽኙ ስርጭት እያስከተለ ያለውንና ሊያስከትል የሚችለውን ሰብዓዊ፣ ማኅበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳቶች ለመቀነስና ለመከላከል የሚያስሉ የተከለከሉ ተግባራትን፣ የሚወሰዱ እምርምጃዎችንና የመብት እገዳዎችን በተመለከተ የሚያብራራ ደንብ አውጥቷል።
በዚህም መሰረት በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ያችላሉ የተባሉ መደረግ ያለባቸውና የተከለከሉ ጉዳዮችን በአዋጁ ማስፈጸሚያ ደንብ በዝርዝር አስቀምጧል። በዚህም መሠረት፡
1. ለሐይማኖታዊ ወይም ማኅበራዊ አላማ፣ ለመንግሥታዊ ወይም ፖለቲካዊ ሥራ ወይም ሌላ መሰል አላማ አምልኮ በሚደረግባቸው ቦታዎች፣ በመንግሥት ተቋማት፣ በሆቴሎች፣ በማናቸውም የመሰብሰቢያ አዳራሾችና ቦታ አራትና ከዚያ በላይ ሆኖ በአንድ ቦታ ላይ መገኘት የተከለከለ ነው።
2. አስገዳጅ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙበት ጊዜ የሚኒስትሮች ኮሚቴ ወይም በኮሚቴው የሚቋቋሙና ውክልና የሚሰጣቸው በክልሎች፣ በከተማና በወረዳ ደረጃ ባሉ ንዑሳን ኮሚቴዎች ስብሰባ እንዲደረግ ሊፈቅድ ይችላል።
3. ማንኛውም ሰው ለሰላምታና ሌላ ማንኛውም አላማ በእጅ መጨባበጥ ክልክል ነው።
4. ማንኛውም አገር-አቋራጭ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥ ሰው በማንኛውም ጊዜ ከተሸከርካሪው ወንበር ብዛት ከ50 በመቶው በላይ ሰዎችን ጭኖ መንቀሳቀስ የተከለከለ ነው።
5. ማናቸውም የከተማ ውስጥ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥ ታክሲ፣ አውቶቡስ፣ የፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት አውቶቡስ ከተሸከርካሪው የወንበር ቁጥር ከ50 በመቶ በላይ ሰዎችን ጭኖ መንቀሳቀስ የተከለከለ ነው።
6. ማንኛውም የግል ተሸከርካሪ ሾፌሩን ሳይጨምር ከተሸከርካሪው የወንበር ቁጥር 50 ከመቶ በላይ ሰዎችን ጭኖ መንቀሳቀስ የተከለከለ ነው።
7. የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ከዚህ በፊት ሲጭን ከነበረው አቅሙ 25 በመቶ በላይ ሰዎችን ጭኖ መንቀሳቀስ የተከለከለ ነው።
8. የኢትዮ-ጂቡቲ የምድር ባቡር ከወንበር ቁጥሩ 50 ከመቶ በላይ ሰዎችን ጭኖ መንቀሳቀስ ተከለከለ ነው።
9. ማንኛውንም ታራሚን ወይም ተጠርጣሪን በአካል በመገኘት በማረሚያ ቤት ወይም በፖሊስ ጣቢያ መጠየቅ ክልክል ነው። [ሆኖም ይህ ድንጋጌ በፖሊስ ጣቢያ ከሚገኝ ተጠርጣሪ ጋር በአካል ሳይገናኙ ስንቅ ማድረስን አይከለክልም]
10.በጭፈራ ቤቶችና በመጠጥ ቤቶች ማናቸውንም የመጠጥና መዝናኛ አገልግሎት መስጠት የተከለከለ ነው።
11.በማናቸውም ቦታ የሺሻ ማስጨስና ጫት ማስቃም መስጠት የተከለከለ ነው።
12. የሲኒማ፣ የቲያትርና በአንድ ቦታ ብዙ ሰዎችን የሚያሰባስቡ መሰል የመዝናኛ አገልግሎቶችን መስጠት ክልክል ነው።
13. ሆቴሎች፣ ካፌዎች ወይም ምግብ ቤቶች አገልግሎት በሚሰጡበት ጊዜ በአንድ ጠረጴዛ ላይ ከሦስት ሰው በላይ እንዲቀመጥ ማድረግ የተከለከለ ሲሆን፤ ተገልጋዮች በሚቀመጡባቸው ጠረጴዛዎቹ መካከል ያለው ርቀትም ሁለት የአዋቂ እርምጃ መሆን አለበት፤ ሆኖም ተገልጋዮች የሚገለገሉት በጠረጴዛ ላይ ካልሆነ በመካከላቸው የሚኖረው ርቀት ሁለት የአዋቂ እርምጃ መሆን አለበት።
14. በድንበር አካባቢዎች በሚገኙ ኬላዎች በኩል ወደ አገር ውስጥ መግባትም ሆነ ወደ ውጪ መውጣት የተከለከለ ነው። [ነገር ግን በውጪ አገር የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በኬላዎች በኩል ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ የሚኒስትሮች ኮሚቴ ፈቃድ ሊሰጥ ይችላል]
15. ፈቃድ ከተሰጠው ሰው ውጪ በማንኛውም የክልልም ሆነ የፌዴራል መንግሥት ባለስልጣን ወይም ባለሙያ ኮቪድ-19ን በተመለከተ የፌዴራል ወይም የክልል መንግሥትን ወክሎ መግለጫ መስጠት የተከለከለ ነው።
16. ከላይ የተጠቀሰው ክልከላ ቫይረሱን አስመልክቶ የወጡ ሕጎችን በተመለከተ የሚደረግ የሙያ ትንተናን ወይም በህክምና ባለሙያዎች የሚደረጉ ማብራሪያዎችን ወይም በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በየዕለቱ የሚሰጡ መረጃዎችን አይመለከትም።
17.ማንኛውም የመኖሪያም ሆነ የንግድ ድርጅት ቤት አከራዮች በተከራዩ ስምምነት ካልሆነ በስተቀር ቤቱን እንዲለቅ ማድረግ ወይም የቤት ኪራይ ዋጋ ጭማሪ ማድረግ የተከለከለ ነው።
18.ማናቸውም በአዋጅ ቁጥር 1156/2011 መሰረት የሚተዳደሩ ሠራተኞችን የሚያስተዳደሩ የግል ድርጅቶች በሥራቸው ያሉ ሠራተኞችን የሥራ ውል ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሚያስቀምጠው ሥርዓት ውጪ ማቋረጥ የተከለከለ ነው።
19.ማንኛውም የመንግሥትም ሆነ የግል ትምህርት ተቋም በትምህርት ቤት ወይም በሌላ ማናቸውም ቦታ አስተማሪና ተማሪዎች በአካል ተገናኝተው መማር ማስተማር ሥራ እንዲሰራ ማድረግ ወይም ማስተማር የተከለከለ ነው።
20.ማንኛውም ሁለትና ከዚያ በላይ ሰው በመሆን የሚጫወቱባቸውን ጨዋታዎች፣ ማጫወትም ሆነ መጫወት የተከለከለ ነው።
21.ማናቸውንም የስፖርት ውድድሮች ወይም የቡድን ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ የተከለከለ ነው።
22. የህፃናት ማጫዎቻ ቦታዎች አገልግሎት መስጠት የተከለከለ ነው።
በተጨማሪም ደንቡ በኮቪዲ-19 ምክንያት ህይወቱ ያለፈ የማንኛውም ሰው የቀብር ሥርዓት የሚፈጸመው በመንግሥት አማካኝነት ለዚሁ አላማ በተለዩ ቦታዎች ሲሆን በቀብሩ ላይ የሚገኘውን የሰው ብዛትና የቀብሩ ዝርዝር አፈፃፀምን በተመለከተ በመመሪያ እንደሚወሰን አመልክቷል።
ይህ የኮቪድ-19 ስርጭትን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 3/2012 ማስፈፀሚያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ተጨማሪ ዝርዝር ነገሮች የያዘ ሲሆን ተፈጻሚነቱም በመላው ኢትዮጵያ ለቀጣዮች አመስት ወራት ይሆናል።














