ነዳጅ አምራች አገራት በኮሮናቫይረስ ምክንያት ምርታቸውን ሊቀንሱ ነው

የነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የነዳጅ አምራች አባል አገራት (ኦፔክ) እና አጋሮቹ በኮሮናቫይረስ ምከንያት አገራት በጣሉት የእንቅስቃሴ ገደብ ምክንያት የተፈጠረውን የፍላጎት መውረድ ተከትሎ የነዳጅ ምርታቸውን በአምስት እጅ ለመቀነስ ተስማሙ።

ቡድኑ በግንቦትና በሰኔ በ10 ሚሊዮን በርሜል በመቀነስ ዋጋው እንዲያንሰራራ እንደሚያደርግ ገልጿል። ከዚያ በኋላም ቀስ በቀስ እአአ እስከ 2022 ድረስ የተቀነሰው ምርት እንዲጨምር ይደረጋል ተብሏል።

ሩሲያን የሚያካትተው ኦፔክ፤ የነዳጅ አምራች አባል አገራትና አጋሮቹን ያቀፈ ሲሆን ሐሙስ ዕለት በቪዲዮ ኮንፍረንስ ስብሰባ ተቀምጦ ነበር።

ሩሲያና ሳኡዲ አረቢያ በዚህ ውይይት ላይ አለመግባባቶች ስለነበሯቸው ፈታኝ ነበር ተብሏል።

ቡድኑና አጋሮቹ 10 ሚሊዮን በርሜል በቀን ወይንም የዓለማችንን አቅርቦት 10 እጅ ለመቀነስ ተስማምቷል።

ተጨማሪ 5 ሚሊዮን በርሜል በሌሎች ነዳጅ አምራች አገራት እንደሚቀነስ ይጠበቃል።

በሐምሌና ኅዳር ወራት መካከል የሚቀነሰው ምርት ወደ 8 ሚሊዮን ዝቅ ሊል ይችላል ተብሏል።

ከዚያም እአአ በታህሳስ 2021 እና ሚያዚያ 2022 መካከል የሚቀነሰው የነዳጅ ምርት ወደ 6 ሚሊዮን ዝቅ እንደሚል ተገልጿል።

የዓለማችን የነዳጅ ዋጋ የነዳጅ አምራች አገራቱ ስምምነት ላይ መድረስ ባለመቻላቸው ምክንያት ባለፈው መጋቢት ወር ወድቆ ነበር።

መጋቢት ላይ በነበረው ስብሰባ ሳኡዲ አረቢያና ሩሲያ ምንም እንኳ የዓለም የነዳጅ ፍላጎት ቢወድቅም የገበያ ድርሻቸውን ለማሳደግ በማሰብ ምርታቸውን ከፍ አድርገው ነበር።

በዚህ ላይ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ካስከተለው የነዳጅ ፍላጎት መውረድ ጋር ተጨምሮ በመጋቢት ወር የመጨረሻ ሳምንት ላይ ከ18 ዓመት ወዲህ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የነዳጅ ዋጋ ወርዷል።

በርግጥ ከዚያ ወዲህ ዶናልድ ትራምፕ ሩሲያና ሳኡዲ አረቢያ ጠባቸውን እንዲያበርዱ ከገሰጹ በኋላ የነዳጅ ዋጋ መጠነኛ መሻሻል አሳይቷል።

ሐሙስ ዕለት የተደረገው የቪዲዮ ኮንፍረንስ አርብ እለት የቡድን 20 አባል አገራት የኃይል ሚኒስትሮች ካደረጉት ስብሰባ ተከትሎ የተካሄደ ነው።

ይህንን ጉባዔ ያስተናገደችው ሳኡዲ አረቢያ ናት።

የሞስኮ ከፍተኛ የነዳጅ ዘይት ተደራዳሪ እና የሩሲያ ዌልዝ ፈንድ የበላይ ኃላፊ ኪሪል ዲሚትሪቭ ለሮይተርስ እንደተናገሩት "ከነዳጅ አምራች አባል አገራት ውጪ ያሉ ይህንን ውሳኔ እንዲቀላቀሉን እንጠብቃለን፤ ይህ ምናልባት ነገ በሚካሄደው የቡድን 20 አባል አገራት ስብሰባ ላይ ይሆናል" ብለዋል።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሳኡዲ አረቢያ የነዳጅ ምርቷን የማትቀንስ ከሆነ ማዕቀብ እንደሚጠብቃት አስጠንቅቀው ነበር።

አሜሪካ ምንም እንኳ ያላት የነዳጅ ምርት እየቀነሰ መሆኑን ብትናገርም የነዳጅ ምርትን የመቀነስ ውሳኔው ግን ተገዥ አይደለችም።

ኮሮና
Banner