"ደስ ብሎኛል፤ የ98 ዓመቷ እናቴ ከኮሮናቫይረስ ድናለች"

የፎቶው ባለመብት, WESLEY SHAH
ዌስሊ ሻህ እባላለሁ። የወ/ሮ ዳፌን ሻህ ወንድ ልጇ ነኝ።
አሮጊቷ እናቴ ወደ ሆስፒታል በተወሰደች ጊዜ፣ በተለይም በኮሮናቫይረስ መያዟን ስሰማ አልዋሻችሁም ለመጥፎ ዜና ራሴን እያዘጋጀሁ ነበር።
አምቡላንሱ መጥቶ ሲወስዳት እውነት ለመናገር በድጋሚ አያታለሁ ሁሉ አላልኩም ነበር።
ሐኪሞቹም ቢሆኑ 99 ዓመት ሊደፍን ወራት የቀሩት ሰው ቫይረሱን ድል ሲመታ አይተው የሚያውቁ አይመስለኝም።
እናቴ ዳፌን መጀመርያ ወደ ናይንዌልስ ሆስፒታል ነበር የተወሰደችው። እዚያም አንድ ሳምንት ለሚሆን ጊዜ የሆስፒታል አልጋ ይዛ ቆይታለች። ከትናንት ወዲያ ሰኞ ለታ ነው ከሆስፒታሉ የወጣችው።
በዚያ ሆስፒታል ምን ተአምር ተፈጥሮ እንደዳነች ለኔም ትንግርት ነው።
የትንፋሽ መርጃ ቬንትሌተር እንኳ አላስፈለጋትም ነው ያሉኝ ሐኪሞቹ። ከሆስፒታሉ ስትወጣ ግን አተነፋፈሷ ትክክል ነበር ማለት አልችልም።
የስኮትላንድ የብሔራዊ ጤና አገልግሎት መኮንኖች ሁልጊዜም ምስጉን ናቸው። አሁን ግን የማይታመኑ ነው የሆኑብኝ።
እናቴን ላለፉት 20 ዓመታት ተንከባክቢያታለሁ። ያም ማለት አባቴ ከሞተ ጀምሮ እንደማለት ነው፡፡ ለዚህን ሁሉ ጊዜ ጤናዋ እክል አልነበረበትም አልልም። ሆኖም የከፋ ነገር ገጥሟት አያውቅም።
በቅርቡ ግን ደረቅ ሳል ስትስልና ትኩሳቷ ሲጨምር ይሄ ነገር ምነድነው ብዬ ሐኪሞች ዘንድ ደወልኩኝ።
የጠረጠርኩት አንዳች የባክቴሪያ ኢንፌክሽን አግኝቷት ይሆናል ብዬ ነው፤ በቃ አንቲባዮቲክ ሰጥተዋት ትድናለች ስል አሰብኩ።
ሆኖም አንቲባዮቲክ ወስዳ ሳይሻላት ሲቀር ይሄ ነገር ምንድነው ብዬ ወደ ሆስፒታል ወሰድኳት።
ከደረቅ ሳሉ በተጨማሪ የምግብ ፍላጎቷ እልም ብሎ ጠፍቶ ነበር። በዚያ ላይ ድካም ይሰማታል።
እናቴ በመጪው ሐምሌ ወር ላይ 99 ዓመቷን ትደፍናለች። እንደምንም 100 ዓመት ሞልቷት ከግርማዊነታቸው ንግሥት ኤልዛቤጥ 2ኛ የቴሌግራም የደስታ መግለጫ እንዲላክላት ከልቤ እመኛለሁ።
ኮቪድ ሕይወቷን ቢያሳጣት ኖሮ ሐዘኔ ቅጥ ያጣ ይሆን ነበር፤ ምክንያቱም እርሷ ጠንካራ ሴት እንደሆነች አውቃለሁ፡፡ ጤንነቷም ለክፉ የሚሰጥም አልነበረም፡፡ በዚህ ሁኔታ ብትሞት ትልቅ ሐዘን ላይ ነበር የምወድቀው።
እርሷ አልጋ በያዘችበት ሆስፒታል አንድም ሰው እንዲጠይቃት አይፈቀድም ነበር። መጀመርያ አካባቢ እናቴ ምን እየሆነ እንዳለ የገባትም አይመስለኝም።
"ልጄ ምነው ቸል አለኝ፤ እንዴት ታምሜ አይጠይቀኝም" ስትል ተገርማ ነበር። በናይንዌልስ ሆስፒታል ነርሶቹ እንደነገሩኝ "እናትህ ደጋግማ ልጄ የታለ? ልጄን ጥሩልኝ!" ትል ነበር።
የጤና ረዳቶቹ ነገሩን ሊያስረዷት ቢሞክሩም ልትሰማቸው የፈቀደች አይመስለኝም።
በቀን ቢያንስ አራት ጊዜ ወደ ሆስፒታሉ እደውላለሁ። በእውነት የጤና ባለሞያዎቹን እንዴት ማመስገን እንዳለብኝ አላውቅም።
አሁን ይህንን የእናቴን ታሪክ ለሚያነቡ ታማሚዎችም ሆኑ አስታማሚዎች የምለው ነገር አለኝ።
"ኮሮና ቫይረስ ክፉ ደዌ ነው፤ ይህ ምንም ጥያቄ የለውም፤ ነገር ግን የ98 ዓመት አሮጊቷ እናቴ ድል ነስታዋለች፤ የምን ተስፋ መቁረጥ ነው ታዲያ!"














