ኮሮናቫይረስ 'አሲዘሽኛል' ብሎ ፍቅረኛውን የገደለው ተጠርጣሪ

በኢሊኖይ ግዛት ነዋሪ የሆኑት ፍቅረኛሞች ሁለቱም ላይመለሱ አሸልበዋል። ለሁለቱም ሞት ምክንያቱ ኮሮናቫይረስ እንደሆነ ፖሊስ ጠርጥሯል።
ቼሪል የፓትሪክ ፍቅረኛው ናት።
ባለፈው ሐሙስ ፓትሪክ ፍቅረኛው ቼሪልን ከጀርባዋ በጥይት ደብድቦ ገድሏታል። እሷን ከገደለ በኋላ ታዲያ ለራሱም አልሳሳም።
ፓትሪክ የ54 ዓመት ጎልማሳ ሲሆን ቼሪል 59 ዓመቷ ነው።
ሬሳቸው በሎክቶፕ ታውንሺፕ አካባቢ በሚገኘው ቤታቸው በተለያየ ክፍል ውስጥ ተገኝቷል።
ሽጉጡ ከፓርትሪክ እጅ አጠገብ የተገኘ ሲሆን የመጀመርያ ዙር ምርመራ ያመላከተው እሱ እሷን ስለመግደሉ ነው።
የፓትሪክ ቤተሰቦች ልጃችን ከደወለ ቆየ፤ በሚል ሪፖርት በማድረጋቸው ነው አስከሬኖቹ ሊገኙ የቻሉት።
የእርሱ ቤተሰቦች ኋላ ላይ በሰጡት ቃል እሱና ፍቅረኛው በኮሮናቫይረስ ሳንያዝ አንቀርም በሚል ስጋት ውስጥ እንደነበሩ መስክረዋል።
ይህ አሳዛኝ ክስተት ከመከሰቱ በፊት ፓትሪክ ኮሮና ቫይረስ ምርመራ አድርጓል። ሆኖም ውጤቱን አልሰማም። ምርመራውን ያደረገው ፍቅረኛው ቼሪል የመተንፈስ ችግር ስላጋጠማት ፈርቶ ነው።
እሷም በተመሳሳይ ምርመራ ያደረገች ሲሆን ውጤቷን ግን ሳትቀበል ነው የተገደለችው።
ምናልባት ምልክቶቿን ሲያይ ኮሮናቫይረስ አሲዛኛለች ብሎ ስላመነ ነው ይህን ግድያ የፈጸመው የሚል ጥርጣሬን ይዟል ፖሊስ።
ፍቅረኛሞቹ አስከሬናቸው ላይ በተደረገ ምርመራ ሁለቱም ከቫይረሱ ነጻ እንደነበሩ ተረጋግጧል።
በሚሊዮን የሚቆጠሩ አሜሪካዊያን ኮሮናቫይረስን ተከትሎ የጦር መሣሪያ ሸምተዋል።
ፖሊስ እንደሚለው በቀን ውስጥ በርካታ የይድረሱልኝ ጥሪዎችን ይቀበላል። ከዚህ ውስጥ የሚበዙቱ የቤት ውስጥ ጥቃቶችን የተመለከቱ ናቸው። ይህም ከኮሮናቫይረስ የቤት መቀመጥ ግዴታ ጋር ተያይዞ የመጣ ነው።
ኢሊኖይ ግዛት እስካሁን 12 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል። ሟቾች ግን 307 ብቻ ናቸው።














