ኮሮናቫይረስ፡ በኢኳዶር ሬሳ-ሳጥን በመጥፋቱ ሬሳ-ካርቶን ታደለ

የሬሳ-ሳጥን በመጥፋቱ የሬሳ-ካርቶን

የፎቶው ባለመብት, AFP

በደቡብ አሜሪካዋ ኢኳዶር የጣውላ ሬሳ ሳጥን እጥረት በመከሰቱ ባለሥልጣናት ለጊዜው የካርቶን ሬሳ ሳጥን እየተጠቀሙ ነው።

በኢኳዶር ሕዝብ እጭቅ ባለባት ከተማ ጓያኪውል እጥረቱ ከፍተኛ በመሆኑ መንግሥት 4 ሺህ የሬሳ "ሳጥኖችን" (የሬሳ ካርቶኖችን) ለማከፋፈል ተገዷል።

የሬሳ መርማሪዎች ምርመራ ከጨረሱ በኋላ የሬሳ ሳጥን ያለህ እያሉ ሲሆን የቀብር አስፈጻሚዎችም ምን ማድረግ እንዳለባቸው ተቸግረው ቆይተዋል።

በዚች የኢኳዶር ትልቅ ከተማ ከሦስት ሚሊዮን ሰዎች በላይ ይኖራሉ። በርካታ ሰዎች በኮሮናቫይረስ እየሞቱም ነው። ምንም እንኳ ይፋዊው የሟቾች ቁጥር 180 ብቻ ነው ቢልም ይህ አሐዝ ትክክል እንዳልሆነ ብዙዎች ያምናሉ።

ፕሬዝዳንት ሌኒን ሞሬኖ ይህ ቁጥር ተመርምረው ኮሮናቫይረስ ተገኝቶባቸው የሞቱትን ብቻ የሚመለከት ነው ብለዋል። የአገሪቱ በቀን የመመርመር አቅም ዝቅተኛ በመሆኑ ዜጎች በቫይረሱ መያዛቸው ሳይታወቅ እየሞቱ እንደሆነ ይገመታል።

ይህቺ ጓያኪውል የምትባለው ከተማ የወደብ ከተማ ስትሆን በሽታው የተነሳባት የኢኳዶር ከተማ ናት። የከተማዋ ነዋሪዎች በየመንገዱ ሬሳ እየተጣለ እንደሆነና መንግሥት ቶሎ ቶሎ ሬሳዎችን እያነሳ እንዲቀብር ሲጠይቁ ነበር።

በርታ ሳሊናስ የተባለች አንዲት ነዋሪ ለቢቢሲ-ስፓኒሽ ክፍል በቅርቡ እንተናገረችው የእህቷ እንዲሁም የእህቷ ባል ሬሳ ከቤት ለማውጣት አራት ቀናት ወስዷል።

ለጊዜው በፕላስቲክ አንሶላ ሬሳዎቹን ጠቅልለን ለማቆየት ተገደን ነበር ብላለች ሳሊናስ ለቢቢሲ።

ኢኳዶር የሕዝቧ ብዛት 17 ሚሊዮን ሲሆን እስካሁን 3ሺህ 465 ሰዎች ቫይረሱ እንዳለባቸው ተረጋግጧል። የጓያኪውል ከተማ ከንቲባ ራሳቸው በቫይረሱ ተይዘው የአልጋ ቁራኛ ናቸው።

ኮሮና
Banner