ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የትዊተር መስራች የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የ1ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ሊያደርግ መሆኑን አስታወቀ
የትዊተርና የመገበያያ መተግበሪያው ስኬዌር መስራች የሆነው ጃክ ዶርሲ፣ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን መከላከልን ለማገዝ የ1 ቢሊየን ዶላን ድጋፍ አደርጋለሁ አለ።
እንደባለጠጋው ዶርሲ ከሆነ ይህ ልግስናው የሀብቱን 28 በመቶ ያክላል።
ጃክ ዶርሲ ይህንን ያስታወቀው በትዊተር ሰሌዳው ላይ ሲሆን፣ "ገንዘቡ በአስቸኳይ አስፈላጊ" መሆኑን ገልጿል።
በርግጥ የትዊተሩ መስራች ዶርሲ ገንዘቡ የኮቪድ-19ን ለመዋጋት በማን በኩል በምን መልኩ እንደሚሰጥ ያለው ነገር የለም።
በአሜሪካ የመተንፈሻ ማሺኖች እንዲሁም የሕክምና ባለሙያዎች የሚያደርጉት መከላከያ አልባሳት እጥረት ያለ ሲሆን በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ እና ግለሰቦችም በገቢ ማጣትና መቀዛቀዝ ክፉኛ ተጎድተዋል ተብሏል።
የ43 ዓመቱ ጃክ ዶርሲ፣ የትዊተርና የስኩዌር የበላይ ኃላፊ ነው።
ጃክ ዶርሲ እንዳለው ስኩዌርር የተሰኘው መተግበሪያ ላይ ያለውን ድርሻ የሚጠቀም ሲሆን ለዚህም በምክንያትነት ያስቀመጠው ከትዊተር ይልቅ ከፍ ያለ የአክስዮን ድርሻ ባለቤት የሆነው ስኩዌር መተግበሪያ ላይ መሆኑን ነው።
በጊዜ ሂደት አክሲዮኖቹ ተሽጠው ለበጎ አድራጎት ተግባሩ የሚውሉ ይሆናል።
አንድ ጊዜ ኮቪድ-19 በቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ ደግሞ ፈንዱ ለሴቶች ጤናና ትምህርት እንዲሁም ለመሰረታዊ ገቢ ጥናት የሚለገስ ይሆናል።
ዶርሲ በትዊተር መልዕክቱ ላይ ገንዘቡን መለገሥ የፈለገው ለውጥ በሚያይበት ቦታ ላይ መሆኑን አስታውቋል።
ሃብቱን ለበጎ አድራጎት ለመስጠት የወሰነው የትዊተሩ ኃላፊ ብቻ ሳይሆን የፌስ ቡኩ ማርክ ዙከበርግም ጭምር ነው።
በቅርቡ ዙከበርግ 30 ሚሊዮን ዶላር በመስጠት ህክምናውን ለማገዝ ቃል ገብቷል።
የአማዞኑ ጄፍ ቤዞስ በበኩሉ 100 ሚሊየን ዶላር በመስጠት በዚህ ወቅት በአሜሪካ በምግብ እጥረት ለሚቸገሩት ለማገዝ እንዲውል ብሏል።
የአፕል ባለቤት ቲም ኩክ ደግሞ በኮሮናቫይረስ ክፉኛ ለተጎዳችው ጣሊያን የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚያደርግ ያስታወቀው ባለፈው ወር ነበር።