ኮሮናቫይረስ፡ ሕይወት እንቅስቃሴ በተገደበባቸው አራቱ የአማራ ክልል ከተሞች ምን ትመስላለች?

በአማራ ክልል ሁለት ግለሰቦች የኮሮናቫይረስ እንዳለባቸው ከተረጋገጠ በኋላ የክልሉ የኮረና ወረርሽን መከላከልና መቆጣጠር ኮማንድ ፖስት የተለያዩ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።

እንደ ኮማንድ ፖስቱ ከሆነ ከመጋቢት 23/2ዐ12 ዓ.ም ከቀኑ 6፡00 ሠዓት ጀምሮ በአዲስ ቅዳም፣ እንጅባራ፣ ቲሊሊና በባህር ዳር ከተሞች ለ14 ቀናት ማንኛውንም ዓይነት የተሽከርካረም ሆነ የህዝብ እንቅስቃሴ እንዳይደረግ ወስኗል።

ለመሆኑ ህዝባዊም ሆነ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ በታገደባቸው ከተሞች ኑሮ ምን ይመስላል? ቢቢሲ የተወሰኑትን አናግሯል።

"የባህር ዳር ከተማ ፀጥ ረጭ ብላለች" አበባው ሃሙስ - አሽከርካሪ ከባህር ዳር

በተሰጠው ውሳኔ መሠረት መኪና አቁሜ ቤት ነኝ። የምኖረው ባህር ዳር አየር ጤና አካባቢ ነው፤ ጸጥ ረጭ ያለ ነው። ብዙም እንቅስቃሴ ም አይታይበትም።

ከኢኮኖሚ አንጻር የሚገኘው የዕለት ገቢ ከመቆሙ ሌላ ምንም ለውጥ የለውም።

በእኔ በኩል እስካሁን ያስቸገረኝ ነገር የለም። ቫይረሱን ከመግታት አንጻር መንግሥት ያወጣውን ተግብረን ቤት አርፈን ቁጭ ብለናል።

ከወቅቱ ሁኔታ አንጻር ምንም የምንፈጥረው ነገር ስለሌለ በአንድ በኩል ውሳኔውን እደግፈዋለሁ

"የያዝነው ሲያልቅ የሚመጣውን አናውቅም" ተገኘ ታረቀኝ - ማሽኖች አምራች ከባህር ዳር

አሁን መቶ በመቶ ሥራ ቆሟል። ለጊዜው ለእኔ ችግር ላይኖረው ይችላል። በስሬ ያሉ ሰራተኞችን ስራ ስላቆምን ግን በቀጣይ ጊዜ ችግር ሊሆን ይችላል።

ደመወዝ መክፈልም ላይኖር ይችላል። ከእኔ ለእነሱ እጨነቃለሁ።

ሥራ የለመድኩ ስለሆንኩ መቀመጥ ከባድ ነው። በውሳኔው መሠረት መውጣት መግባት ሰለማይቻል ንብረት መጠበቅም አልቻልንም።

የያዝነው ሲያልቅ የሚመጣውን አናውቅም እንጂ ባለችው ነገር ተዘጋጅተናል።

" ውሃ በወር አንድ ጊዜ የማናገኝበት ሁኔታ አለ" ዘላለም ታምሩ ኮሙኒኬተር ከእንጅባራ

አንጅባራ እና አካባቢው ላይ ኮማንድ ፖስቱ እንቅስቃሴ ካገደ በኋላ ዛሬ አልፎ አልፎ ከተፈቀደላቸው ውጭ አስቤዛ ለሟሟላት እና ከገጠር መረጃ ሳይኖራቸው ከመጡት ውጭ እንቅስቃሴ የለም።

አሁን ቤት ነን። ንክኪ የለም። ሁሉም ቤት ዘግቶ ነው ያለው። ህብረተሰቡ የተጠረጠሩ ሰዎችን እየጠቆመ ግዴታውን እየተወጣ ነው ነው።

አሁን ስጋት የለኝም ቤት ስላለሁ። አንገብጋቢ ነገር ገጥሞኝ ከቤት ወጣሁ ጓንት፣ ጭንብል እና አልኮልም እየተጠቀምኩ ነው የምንቀሳቀሰው። ቫይረሱ አስቸጋሪ በመሆኑ ነው ቤት የተቀመጥነው።

እንጅባራ ላይ መብራት እና ውሃ ችግር ነው። ውሃ በወር አንዴ የማናገኝበት ሁኔታ አለ። ንጽህናችሁን ጠብቁ ከመባሉ አንጻር ይኼ ትንሽ አስቸጋሪ ነው ።

በውሳኔው ተከራይተው የሚኖሩ እና አብሰለው የማይበሉ እየተቸገሩ ነው። እነዚህ ግለሰቦች በየሆቴሉ ፈርመው የሚበሉ ነበሩ። ፈርመው ስለሚበሉ የሚሄዱበት የለም። ለእነዚያ ግብረ ሃይሉ አስቤዛ እንዲያሟሉ እያደረገ ነው። ግን በጣም የከፋ ነው ማለት አይቻልም