ኮሮናቫይረስ፡ ለኅዳር በሽታ ያልተበገሩት የ108 ዓመቷ አዛውንት ለኮሮና እጅ ሰጡ

የፎቶው ባለመብት, FAMILY PHOTO
የኅዳር በሽታ በድሮ ጊዜ የነበረ ነው። ፈረንጆቹ ስፓኒሽ ፍሉ ወይም ግሪፕ ይሉታል። በኦሮምኛ ተናጋሪዎች ዘንድ ደግሞ ዱ'ኩባ ቂሌንሳ ወይም የንፋስ በሽታ ይባል ነበር።
የአንደኛውን የዓለም ጦርነት ፍጻሜ ተከትሎ ዓለምን ጉድ ያደረገ መቅሰፍት ነው።
ያን ጊዜ በሕይወት ነበሩ፣ እንግሊዛዊቷ ወ/ሮ ሂልዳ ቸርችል። የዓለምን ሕዝብ በሚሊዮኖች የቀጠፈው ይህን በሽታ በድል የተወጡት እኚህ አይበገሬ ሴትዮ በመጨረሻም ለኮሮናቫይረስ እጅ ሰጥተዋል።
እማማ ሂልዳ የሞቱት በታላቋ ብሪታኒያ ኦክስፎርድ ከተማ በፎልድ ኬንዮን ሎጅ የጡረተኞች ማዕከል ውስጥ ቅዳሜ ዕለት ነው።
እማማ ሂልዳ ለአራት ቀናት የኮቪድ-19 መለስተኛ ምልክቶች ታይተውባቸው በኮሮናቫይረስ ከተያዙ በኋላ ነው ሕልፈታቸው ማለፉ ድንገት የተሰማው።
የልጅ ልጃቸው ሚስተር ዊል ሃድኮፍት "አያቴ ልበ-ቀናና የቤተሰባችን ዋልታና ማገር ነበሩ" ሲል በሐዘን ልብ ለቢቢሲ ተናግሯል።
በ108 ዓመታቸው የሞቱት እማማ ሂልዳ ቅዳሜ ባይሞቱ ኖሮ 109 ዓመት ልደታቸው በነገታው እሑድ ሊከበርላቸው ዕቅድ ተይዞ ነበር።
"በእውነቱ ልባችን ተሰብሯል፤ በተለይ ለልደቷ አንድ ቀን ሲቀራት መሞቷ ድርብ ሐዘን ነው፤ ለዘላለሙ እንናፍቃታለን›› ብሏል የልጅ ልጃቸው አቶ ዊል ሃድክሮፍት።
የልጅ ልጃቸው ሃድክሮፍት ራሳቸው ዕድሜያቸው የዋዛ አይደለም። 50 ዓመታቸው ነው።
እማማ ሂልዳ 4 ልጆች፣ 11 የልጅ ልጆች፣ 12 የልጅ ልጅ ልጆችና 3 የልጅ ልጅ ልጅ ልጆችን አይተዋል።
እማማ ሂልዳ በሰፈር መኪና ሲያልፍ "እኒህ ሀብታም መሆን አለባቸው" ይባል በነረበት ዘመን የነበሩና፤ ለመጀመርያ ጊዜ አውሮፕላን ክንፍ አውጥቶ ሲበር እንደተመለከቱ የልጅ ልጃቸው መስክረዋል።
እማማ ሂልዳ የአንደኛውንም ሆነ የሁለተኛውን የዓለም ጦርነት ተመልክተዋል።
የኅዳር በሽታ በኢትዮጵያ
የኅዳር በሽታ እንደ ጎርጎሮሲያዊያኑ ከ1918 ጀምሮ ለሁለት ዓመታት የዘለቀና በመላው ዓለም 50 ሚሊዮን ሰዎችን የፈጀ መቅሰፍት ነበር። ያኔ ድሮ የእማማ ሂልዳን ታላቅ እህትም የገደለው ይኸው ወረርሽኝ ነበር።
በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1911 ይህ መቅሰፍቱ ወደ አገራችን በኅዳር ወር በመግባቱ በተለምዶ የኅዳር በሽታ በሚል ይታወቃል። ቸነፈር ብለው የሚጠሩትም አሉ።
በወቅቱ በተለይ በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቀባሪ እስኪያጡ ድረስ በቀን እስከ 300 ሰዎች ይሞቱ እንደነበር በታሪክ ተጽፏል። በሽታው ከኅዳር 7-20 ድረስ ለ14 ቀናት ብቻ ቢዘልቅም በሺህ የሚቆጠሩ አዲስ አበባዊያንን ፈጅቷል።
ከመኳንንቱ መካከልም ከንቲባ ወሰኔ ዘአማኑኤልም በዚሁ ወር እንደሞቱም ይነገራል።
አንዳንድ ታሪክ ጸሐፍት ስለዚህ በሽታ ልዩ ነገር ሲዘግቡ "የተያዘው ሰው በ5ቀናት ውስጥ ወይ ይሞታል ወይ ይሽራል›› ሲሉ ጽፈዋል።














