የኮሮናቫይረስ ስርጭትና አንዳንድ የኢትዮጵያ ሆስፒታሎች ያሉባቸው ተግዳሮቶች

የሆስፒታል አልጋዎች

የፎቶው ባለመብት, Arterra

የኮሮናቫይረስ ሥርጭትን ለመግታት እንዲችሉ ሆስፒታሎች ያሉባቸውን ጫናዎች ለማቅለል ያሰችላል ያሏቸውን እርምጃዎችን እየወሰዱ ነው።

ከእነዚህ መካከልም፤ መጨናነቆችን ለመቀነስ ተመላላሽ ታካሚዎችና ጊዜ የሚሰጡ ሕመም ያለባቸው ሰዎች ባሉበት አካባቢ ባሉ ጤና ጣቢያዎች አገልግሎት እንዲያገኙ፣ የአስታማሚ ቁጥሮችን መቀነስ፣ የእጅ ንፅህና መጠበቂያዎችን ማቅረብ እና ለይቶ ማቆያዎችን ማዘጋጀት ይገኙበታል።

ይህንን በተመለከተም በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ሆስፒታሎች እያደረጉ ስላለው ዝግጅት ጠይቀናል።

ፈለገ ሕይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል

የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተሩ ዶ/ር የሰውበላይ ምናለ ሆስፒታሉ ከዚህ በፊት ሲጠቀምባቸው የነበሩ የፊት መሸፈኛ ጭንብልና ጓንቶች መኖራቸውን ገልፀው፤ እስካሁን የእነዚህ ግብዓት ችግር እንዳልገጠማቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ በሆስፒታሉ ውስጥ በተዘጋጀ ለይቶ ማቆያ ውስጥ በቫይረሱ ተጠርጥረው የሚገቡ ሰዎችን ክትትል ለማድረግ ግን ቫይረሱን ለመከላከል ተብሎ የሚለበሰው ሙሉ የህክምና ልብስ እንደሌላቸው ገልፀዋል።

ሆስፒታሉ ከዚህ ቀደም የኦክስጅን እጥረት እንደነበረበት ያነሳንላቸው ዶ/ር የሰውበላይ፤ የአማራ የኦክስጅን ማምረቻ በመኖሩ የሚያጋጥም ችግር ቢኖርም አሁን ባለው ሁኔታ ቶሎ ማዘጋጀት እንደሚቻል ገልፀው፤ ለወደፊቱ ግን ምርቱን መጨመር እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ደሴ ሪፈራል ሆስፒታል

የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ኑርዬ ሀሰን እንደገለፁልን፤ የኮሮናቫይረስ ሥርጭትን ለመግታት የደሴ ሪፈራል ሆስፒታል ካሳለፋቸው ውሳኔዎች መካከል፤ እድሜያቸው ከ55 በላይ የሆኑና የተለያዩ አባባሽ ህመሞች ያሉባቸው የጤና ባለሙያዎች ለሁለት ሳምንት እረፍት እንዲወስዱ ማድረግ ነው።

ሜዲካል ዳይሬክተሩ እንደሚሉት የባለሙያ እጥረት እንዳይከሰትም የማሸጋሸግ ሥራዎች ተከናውነዋል።

ይሁን እንጅ የንፅህና መጠበቂያ የሚውል አልኮል ቢኖርም፤ ለጤና ባለሙያዎች የሚሆኑ የፊት ጭንብሎች እጥረት ግን ከፍተኛ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ሆስፒታሉ ከዚህ በፊት ከመድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ የገዛቸውንና ከአንድ ጊዜ በላይ አገልግሎት ላይ የማይውሉ ጭንብሎችን ከባዶው ይሻላል በማለት በድጋሚ ለመጠቀም መገደዱን ዶ/ር ኑርዬ ገልጸዋል።

መደወላቡ ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል

በመደወላቡ የኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል አጠቃላይ ሐኪምና መምህር የሆኑት ዶ/ር ኦላና ዋቆያ በሆስፒታሉ በኮሮናቫይረስ የተጠረጠሩ ሁለት ሰዎችን ውጤት እየተጠባበቁ መሆኑን ገልፀው፤ ለባለሙያዎች እንደ ጭምብልና ጓንት ያሉ የህክምና ቁሳቁስ እጥረት መኖሩን ለቢቢሲ አስረድተዋል።

በቫይረሱ ከተጠረጠሩት ታካሚዎች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ላላቸው ባለሙያዎችም ሆነ በአጠቃላይ የሆስፒታሉ ባለሙያዎች ራሳቸውን ለመጠበቅ የሚያስችሉ ቁሳቁሶች የሉም ብለዋል።

"አንዴ ተጠቅመን ማስወገድ ያለብንን የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ (ጭንብል) ለሳምንት ያህል እየተጠቀምን ነው" ሲሉም ያለውን ችግር ገልጸዋል።

ይህንንም አጥተው ያለምንም መከላከያ የሚሰሩ ባለሙያዎች መኖራቸው ትልቅ ስጋት ነው ብለዋል።

አርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል

የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ተመስገን ተሾመ በሆስፒታሉ በኮሮናቫይረስ የተጠረጠሩ ሰዎች በከተማው ወደተዘጋጀው ለይቶ ማቆያ እስከሚገቡ ድረስ ለሁለት ሰዓታት ያህል የሚያቆዩበት ቦታ መኖሩን ገልፀውልናል።

በሆስፒታሉ ሌሎች ታካሚዎች በመኖራቸው ተጠርጣሪዎቹ ከዚህ ሰዓት በላይ እንዲቆዩም አይደረጉም ብለዋል።

በቫይረሱ የተያዘ ሰው ቢገኝና የመተንፈሻ ችግር ካለበት አጋዥ የመተንፈሻ መሳሪያ (ቬንትሌተር) የተወሰነ በሆስፒታሉ ቢኖርም፤ የታማሚ ቁጥር እየጨመረ ከመጣ ግን እጥረት ሊያጋጥም ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ነግረውናል።

እነዚህ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል ለሕዝቡ የህክምና አገልግሎት የሚሰጡ ሆስፒታሎች የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ቢከሰት ህሙማንን ለማከምና ለመንከባከብ የሚያስፈልጉ መሰረታዊ ቁሳቁሶች እጥረት እንዳለባቸው አመልከተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በጽህፈት ቤታቸው በኩል ዛሬ ባወጡት መግለጫ ላይ እንዳመለከቱት "የመከላከያና የሕክምና ቁሳቁሶችን በየቦታው ለማዳረስ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል" ብለዋል።

ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፌደራልና የክልል አካላትም በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚያስፈልጉ መገልገልገያዎችንና መድኃኒቶችን ለማሟላት ጥረት እያደረጉ እንደሆነ ቢናገሩም፤ ባለሙያዎቹ ግን አቅርቦቶቹን በአፋጣኝ ማግኘት ካልቻሉ ሊፈተር የሚችለው ችግር እያሳሰባቸው መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ኮሮና
Banner