የአሊባባ ባለቤት ቻይናዊው ባለጸጋ ጃክ ማ አሜሪካንን ረዳ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቻይናዊዉ ባለጸጋ የጭምብልና የኮሮናቫይረስ መመርመሪያ መሳሪያዎቹን ወደ አሜሪካ ልኳል።
ባለሃብቱ የምርመራ መሳሪያዎቹና ጭምብሎች ሲጫኑ የሚያሳዩ ሁለት ምስሎችን በትዊተር ገጹ ላይ አስፍሯል።
በዚህ ወር መጀመሪያ አካባቢ 5 መቶ ሺህ የመመርመሪያ መሳሪያዎችንና 1 ሚሊዮን ጭምብሎችን ወደ አሜሪካ እንደሚልክ ተናግሮ ነበር።
ዓለም አቀፍ ትብብር ያስፈልገናል በማለት ቀደም ሲል ወደ አውሮፓም ተመሳሳይ የኮሮናቫይረስ የቅድመ መከላከያ መሳሪያዎችን ልኳል ጃክ ማ።
አሁን ወደ አሜሪካ የተጫነው የእርዳታ መሳሪያም ባለፈው ሳምንት ጃክ ማ ፋውንዴሽንና አሊባባ ፋውንዴሽን 5 መቶ ሺህ የምርመራ መሳሪያዎችንና 1 ሚሊዮን ጭምብሎችን ወደ አሜሪካ ለመላክ ተዘጋጅተናል ማለታቱን ተከትሎ የተፈጸመ ነው።
ከአሁን በፊትም ተመሳሳይ እርዳታ ለጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ጣሊያን፣ ኢራንና ስፔን የረዳ ሲሆን በመላው አውሮፓ የሚሰራጩ 2 ሚሊዮን ጭንብሎችንም እንደሚያከፋፍል ቃል ገብቷል።
ጃክ ማ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ሰዎችን በመቀላቀልም ኮሮናቫይረስን ለመከላከል ተጨማሪ ምርምሮች እንዲከካሄዱ እየደገፈ ይገኛል።
የማይክሮሶፍት መስራቹና የዓለማችን ሁለተኛው ሃብታም ሰው ቢል ጌትስ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በቢል እና ማሊንዳ ፋውንዴሽን በኩል 100 ሚሊዮን ዶላር መድበዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ቢል ጌትስ ከቦርድ ኃላፊነታቸው ወርደው በጤናና መሰል የበጎ አድራጎት ሥራዎች መቀጠል እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
የቻይና ሌሎች በርካታ ባለሃብቶችም ኮሮናቫይረስን ለመከላከል ገንዘባቸውን ፈሰስ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።












