በህንድ የአንድ ህንጻ ነዋሪዎች በውሃ ቧንቧቸው አረቄ መፍሰሱ ደንጋጤን ፈጥሮባቸዋል

በህንድ አንድ ከተማ ውስጥ የአንድ ህንጻ ነዋሪዎች ከቧንቧቸው የአረቄ እና የቢራ ቅልቅል የሆነ አልኮል መፍሰሱ ደንጋጤን ፈጥሮባቸዋል።

ባሳለፍነው ሰኞ ነበር ኬራላ በምትሰኘው የህንድ ከተማ በሚገኝ አንድ የመኖሪየ ህንጻ ላይ ከፍተኛ ጠረን እና ቡኒ ቀለም ያለው መጠጥ ከግለሰቦች ቧንቧ መፍሰስ የጀመረው።

ነዋሪዎቹ የገጠማቸውን ነገር በፍጥነት ለሚመለከተው የመንግሥት ቢሮ ካስታወቁ በኋላ፤ የሚጠቀሙት የውሃ ጉድጓድ በመንግሥት መስሪያ ቤት በስተት መበከሉን ተረድተዋል።

ነዋሪዎቹ የውሃ አቅርቦት ከሚያገኙበት የውሃ ጉድጓድ አቅራቢያ በመንግሥት የተወረሰ 6ሺህ ሊትር አልኮል ተቀብሮ ኖሯል።

በፍርድ ቤት ትዕዛዝ በትልቅ ጋን ተደርጎ እንዲቀበር የተደረገው አልኮል በአቅራቢያ ከሚገኘው የውሃ ጉድጓድ ጋር ተቀላቅሎ ነበር።

"በጣም ነበር የተደናገጥነው" ሲል በህንጻው ላይ የሚኖረው ጆጂ ማላኢካል ለቢቢሲ ተናግሯል። "ውሃው በጣም ይሰነፍጥ እና ቡኒ ቀለም ስለነበረው ለይተነዋል" ብሏል።

የአከባቢው ባለስልጣናት የተፈጸመውን ስህተት ለማረም የውሃ ጉድጓዱን ማጽዳት እና በንጹህ ውሃ መሙለት የሚጠበቅባቸው ሲሆን፤ ይህንንም ለመከወን እስከ አንድ ወር ሊወስድባቸው ይችላል ተብሏል።

እስከዚያው ባለስልጣናቱ በየቀኑ 5ሺህ ሊተር ውሃ ለነዋሪዎቹ እያቀረቡ እንደሆነ ተነግሯል።