የሌሴቶ ቀዳማዊት እመቤት የባሏን የቀድሞ ሚስት በመግደል ወንጀል ፍርድ ቤት ልትቀርብ ነው

የሌሴቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ከባለቤታቸው ጋር

የፎቶው ባለመብት, AFP

የሌሴቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ባለቤት ቀዳማዊት እመቤት ሜይሳያህ ታባን የባሏን የቀድሞ ባለቤት በመግደል ወንጀል ፍርድ ቤት ልትቀርብ ነው።

ከሰሞኑ ቀዳማዊቷ እመቤት ሜይሳያህ ታባን በደቡብ አፍሪካ ለፖሊስ እጇን ሰጥታለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቶማስ ታቤንም በግድያው ዙሪያ ከፖሊስ ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀድሞ ባለቤት ሊፖሌሎ ታቤን በሌሴቶ መዲና ማሴሮ በሚገኘው ቤቷ በጥይት ተተኩሶባት የተገደለችው ከሦስት ዓመት በፊት ነበር።

በወቅቱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለበዓለ ሲመታቸው ሁለት ቀናት ይቀራቸው ነበር ግድያው የተፈጸመው ተብሏል፤ መረር ያለ የፍች ሂደትም ላይ ነበሩ።

ግድያውን የፈፀሙት ያልታወቁ ታጣቂዎች ነበር ቢባልም በቅርቡ የፖሊስ ኮሚሽነር ሆሎሞ ሞሊቤ ለፍርድ ቤት ያቀረቧቸው አዳዲስ መረጃዎች ጥያቄዎችን አጭረዋል።

ፖሊስ የአርባ ሁለት ዓመት እድሜ ያላትን የአሁኗን ባለቤታቸውን ጠርጥሬያለሁ ማለቱን ተከትሎ፤ ቀዳማዊቷ እመቤት ጠፍታ ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቶማስ ታባኔ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ፖሊስም በምላሹ የእስር ማዘዣ አውጥቶ ደቡብ አፍሪካ በመሄድ ከጠበቃዎቿና ከፓሊስ ጋር በተደረገ ድርድር ራሷን አሳልፋ መስጠቷን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

የፖሊስ ኮሚሽነር ሆሎሞ ሞሊቤሊ ለቢቢሲ እንዳሳወቁት በአሁኑ ሰዓት በፓሊስ ቁጥጥር ስር እንዳለችና በዛሬው እለትም ፍርድ ቤት እንደምትቀርብ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍርድ ቤት ሄደው የዋስ መብቷ እንዲከበር ይጠይቃሉ የሚለው ግልፅ ባይሆንም፤ ፖሊስ ኮሚሽነሩ ግን ቀዳማዊት እመቤቷ ልትሰወር ስለምትችል የዋስ መብቷ እንዳይከበር እንደሚሟገቱ ጨምረው አስረድተዋል።

የቀዳማዊቷ እመቤት ጠበቃ ሬታቢሌ ሴትሎጆአኔ በበኩላቸው ምንም አይነት አስተያያት አልሰጥም በማለት ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ባለፈው ወር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከግድያው ጋር በተያያዘ በፖሊስ መጠየቃቸውን ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ የተቃዋሚ ደጋፊዎች በመዲናዋ ማሴሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን እንዲለቁ በሰልፍ ጠይቀዋል።

የተቃዋሚዎች ግፊት በመጨመሩም ስልጣን እንደሚለቁ ቢያሳውቁም መቼ ሊሆን እንደሚችል አላሳወቁም።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለቤታቸውም ሆነ እሳቸው የተወነጀሉበትን ወንጀል ከማንሳት ተቆጥበው በጡረታ ራሴን አገልላሁ ብለዋል።

አገሪቷን እያስተዳደረ ያለውና ተቃዋሚው ፓርቲ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለቀድሞ ባለቤታቸው ግድያ ወንጀል ምርመራ እንቅፋት ሆነዋል ይሏቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ የአሁኑ ባለቤታቸው ምንም አይነት አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።