ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አባቱ በኮሮናቫይረስ ተጠርጣሪነት ወደ ለይቶ ማቆያ የገባበት ቻይናዊ አካል ጉዳተኛ ታዳጊ ሞተ
በራሱ መንቀሳቀስም ሆነ ምንም አይነት ነገሮችን ማከናወን የተሳነው ቻይናዊ ታዳጊ፤ አባቱ በኮሮናቫይረስ ተጠርጣሪነት ተለይቶ ማቆያ ውስጥ እንዲገባ በተደረገ በሳምንቱ ህይወቱ አልፏል።
አባትየው ለታዳጊው ብቸኛው አሳዳጊ እንዲሁም ተንከባካቢው ነበር ተብሏል። ይህንንም ተከትሎ ቻይና ሁለት ባለስልጣኗቿን ከሥራ አባራለች።
የአስራ ስድስት ዓመቱ ታዳጊ ሞቶ የተገኘው ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ዕለት ሲሆን አባቱ እንዲሁም ወንድሙ በለይቶ ማቆያ ውስጥ ከገቡ ከሳምንት በኋላ ነው።
የታዳጊው ህይወት ከማለፉ በፊት በሳምንት ውስጥ ሁለት ጊዜ ብቻ እንደተመገበም የወጡ ሪፖርቶች ያሳያል።
የአካባቢው የኮሚዩኒስት ፓርቲ ፀሐፊ እንዲሁም ከንቲባ ሁጃሄ ከስልጣናቸው እንዲወርዱ ተደርገዋል።
የታዳጊውም ታሪክ በማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዘንድ መነጋገሪያ ሆኗል።
ቤተሰቡ የኮሮና ቫይረስ መነሻ ናት በምትባለው ሁቤይ ግዛትም ይኖሩ ነበር።
አባትየው ለይቶ ማቆያ ውስጥ ከገባ በኋላ ዌይቦ ተብሎ በሚጠራው የቻይና ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ልጁ ብቻውን እንደሆነ፣ ምግብም ሆነ ውሃ ቤት ውስጥ እንደሌለ በመግለጽ እርዳታ እንዲሰጠው መማፀኑን የሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
'ሰረብራል ፐልሲ' ተብሎ በሚጠራውና ገና በጨቅላነት በሚከሰት በሽታ ይሰቃይ የነበረው ታዳጊ የእይታ ችግር፣ የመስማትና የመናገር እክል፣ የጡንቻ መዛል በአጠቃላይ አካላዊ እንቅስቃሴን ማድረግ አይችልም ነበር ተብሏል።
ታዳጊው መሞቱ ከተሰማ በኋላ ባለስልጣናቱ ምርመራ እንደሚጀምሩ አሳውቀዋል።
እስካሁን ባለው መረጃ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 17 ሺህ የደረሰ ሲሆን ለ361 ሰዎች ህይወት መቀጠፍም ምክንያት ሆኗል።
ከቻይና ውጭ 150 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውም የተረጋገጠ ሲሆን በፊሊፒንስም አንድ ሞት ተከስቷል።
የዓለም ጤና ድርጅት ቁጥሩ ከዚህ በላይ እንደሚያሻቅብም ያስጠነቀቀ ሲሆን፤ የቻይና ባለስልጣናት ቫይረሱ እንዳይዛመት የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ናቸው።