የአውስትራሊያ እሳት፡ በሺዎች የሚቆጠሩት እሳት ሽሽት ወደ ውሃ ዳርቻዎች ተሰደዱ

የፎቶው ባለመብት, PETER HOSKIN
በአውስትራሊያ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተነሳውን የሰደድ እሳት ለማምለጥ ወደ ባህር ዳርቻዎች ተሰደዋል።
እሳቱ ወደ የቪክቶሪያ ባህር ዳርቻ ከተማ ወደ ሆነችው ማላኮታ የተዛመተ ሲሆን ፤ ወደ መኖሪያ ቤቶችም እየገሰገሰ ነው። የአካባቢው ነዋሪዎች፤ ደም በለበሰው ሰማይ ሥር በውሃ ዳርቻዎች ላይ መጠለልና ጀልባዎች ላይ ተሳፍሮ መቆየት "በጣም ፈታኝ ነው" ሲሉ ያሉበትን ሁኔታ ገልፀውታል።
በደቡብ ዌልስ ሌላ ሁለት ሰዎች መሞታቸውንም ባለሥልጣናት አረጋግጠዋል። እስካሁን በአገሪቷ ከተከሰተው ሰደድ እሳት ጋር ተያይዞ 12 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል።
በሲድኒና ሜልቦርን መካከል በርካታ በዓል ወደ ሚከበርባቸው ቦታዎች የሚወስዱ መንገዶች በእሳት አደጋው ምክንያት ተቋርጠዋል።
በሁለት አውስትራሊያ ግዛቶች፤ ከደቡብ ዌልስ ባቴማስ ቤይ፤ ወደ ቪክቶሪያ ቤርንስዳሌ በ500 ኪሎ ሜትር በአደገኛ ሁኔታ እየተስፋፋ ነው።
የአባት እና ልጅ እንደሆነ የተነገረ የሁለት ሰዎች አስክሬን በኒው ደቡባዊ ዌልስ ኮባርጎ ከተማም ተገኝቷል።
የደቡብ ዌልስ ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጋሪይ ወርቦይስ " በጣም አሳዛኝ አጋጣሚ ነው፤ እሳቱ ወደ እነርሱ ከመዛመቱ በፊት ግለሰቦቹ የሚቻላቸውን አድርገዋል"ብለዋል።
ባለሥልጣናት እንዳሉት በአካባቢው ሌሎች አምስት ሰዎች የደረሱበት አልታወቀም። ከእነዚህ መካከል አራቱ ከቪክቶሪያ፤ ሌላው ደግሞ ከኒው ደቡባዊ ዌልስ ነው።
የቪክቶሪያ ግዛት አስተዳዳሪ ዳንኤል አንድሪውስ እንዳሉት በአካባቢው ዋና አውራ ጎዳና በመዘጋቱ፤ አገልግሎት ለተቋረጠባቸው አካባቢዎች ምግብ፣ ውሃ እና ኃይል ለማድረስ መርከብ ሊጠቀሙ እንደሚችሉ አስታውቀዋል።
"እነዚህ ተነጥለው ያሉ ማህበረሰቦች የባህር ኃይልን በመጠቀም መድረስ ይቻላል" ሲሉም አክለዋል።
ባለሥልጣናት በአብዛኛው ጎብኝዎች የሆኑና በአካባቢው ያሉ ሰዎች አሁን አካባቢውን ለቆ ለመውጣት ስለረፈደና አደገኛ ስለሚሆን ባሉበት እንዲቆዩ አሳስበዋል።
እነዚህ ማህበረሰቦች በሚኖሩበት ሰሜናዊ ግዛት፤ እሳቱ በአካባቢው ባለው ሙቀት ፣ ንፋስና ደረቅ መብረቅ የአየር ጠባይ ሳቢያ እየተስፋፋ መሆኑም ተነግሯል።















