አውስትራሊያ፡ በእሳትና ከባድ ሙቀት ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታወጀ

የእሳት አደጋ ተከላካዮች

የፎቶው ባለመብት, EPA

በአውስትራሊያዋ ኒው ሳውዝ ዌልስ በታሪክ እጅግ ከባድ በተባለ ሙቀትና የደን ቃጠሎ ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ ታውቋል።

በአውስትራሊያ ታሪክ ተመዝግቦ የማይታወቅ ነው የተባለው ሙቀት ባሳለፍነው ማክሰኞ 40.9 ዲግሪ ሴንቲግሬድ የደረሰ ሲሆን የሀገሪቱ ዜጎች ደግሞ ተቃጠልን፤ የዓለም መጨረሻ ቀርቧል መሰል ሲሉ ነበር።

ነገር ግን በሳምንቱ መጨረሻ እንደውም የባሰ ከባድ ሙቀት ሊመዘገብ እንደሚችልና ሰደድ እሳቱ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚችል ባለሙያዎች አስጠንቅቀዋል።

የኒው ሳውዝ ዌልስ ባለስልጣናት በአሁኑ ሰአት በተለያዩ ቦታዎች የተከሰቱ 100 እሳቶችን ለማጥፋት ደፋ ቀና እያሉ ሲሆን ሰደዱ ሃገሪቱን ማመስ ከጀመረ አንድ ወር አልፎታል።

ዛሬ ጠዋትም ግዛቲቱ አስተዳዳሪ ግላዲስ ቤሬጂክሊያን እየተባባሰ ከመጣው እሳትና ከባድ ሙቀት ዜጎችን ለመታደግ በማሰብ ለሰባት ቀናት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጀዋል።

በአውስትራሊያ በተደጋጋሚ የሚከሰቱት የዱር እሳት፣ ድርቅና ከባድ ሙቀት ሀገሪቱ ከአየር ጸባይ ለውጥ ጋር በተያያዘ ያላት ቁርጠኝነት ደካማ መሆኑን ማሳያ ሊሆን ይችላል ብለው የሚተቹም አልጠፉም።

ከባድ ሙቀት ከየትኛው ተፈጥሮአዊ አደጋ በበለጠ በአውስትራሊያ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች ሞት ምክንያት ነው።

ለዚህ ሁሉ መከራ መነሾው የሕንድ ውቅያኖስ ዲፖሌ (IOD) ሚቲዮሮሎጂካዊ ክስተት ሲሆን ውቅያኖሱን በሚጎራበቱና በምድር ወገብ አቅራቢያ ባሉ ሀገራት የዝናብ ስልትን ይቀይራል።

ይህም ከምስራቅ አፍሪካ እስከ ኢንዶኔዢያ ድረስ የተለጠጠ ሲሆን የአየር ጠባዩ እስከ አውስትራሊያ ድረስ ርቆ ይስተዋላል።

አውስትራሊያ ከባድ ድርቅ እና ሰደድ እሳት ሊከሰት እንደሚችል መረጃው ቢደርሳትም ምንም ማድረግ አልቻለችም። በያዝነው ሳምንትም ከባዱ ሙቀት ተባብሶ በመቀጠል እስከ 45 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሊደርስ ይችላል ተብሏል።

እስካሁን በአውስትራሊያ በክስተቶቹ ምክንያት ስድስት ሰዎች ሲሞቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤቶች ደግሞ ከጥቅም ውጪ ሆነዋል። በሚሊየን የሚቆጠር ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ደንም ወድሟል።