የተትረፈረፈ ቢመስልም የአሸዋ እጥረት ዓለም ላይ ተፈጥሯል

የፎቶው ባለመብት, GUILLAUME SOUVANT
በተለይም በበረሃና በባህር ዳርቻዎች የሚገኘው አሸዋ የትም የሚገኝ ቢመስልም በዓለም ላይ ሰዎች እጅጉን እየተጠቀሟቸው ካሉ ነገሮች ሁለተኛው ነው።
ባለፈው መስከረም ወር ብቻ ደቡብ አፍሪካዊ ሥራ ፈጣሪ፣ ሁለት ህንዳዊያን እንዲሁም ሜክሲኳዊ የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋች ብዙ ዋጋ ባልተሰጠው ነገር ግን በጣም አስፈላጊ በሆነው አሸዋ ምክንያት ተገድለዋል።
ብዙም ባይመስልም አሸዋ እጅጉን አስፈላጊ ነገር ነው። በጥቅሉ ለከተሞች ግንባታ ወሳኝ ግብአት ነው- አሸዋ። የገበያ ማዕከሎች፣ የጋራ መኖሪያ ቤቶች፣ የአስፓልት መንገዶች ግንባታ ያለ አሸዋ የሚታሰብ አደለም።
በየቦታው የሚታዩት የመስታወት መስኮቶች፤ የስማርት ስልኮች ስክሪን ጭምር ከቀለጠ አሸዋ የሚሰሩ ናቸው። በስልኮቻችን እንዲሁም በኮምፒውተሮቻችን ውስጥ ያሉ ሲልከን ቺፖችም ከቀለጠ አሸዋ የተሰሩ ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, Ernie Janes / Alamy Stock Photo
ይህም ብቻ አይደለም በመኖሪያ ቤቶቻችን ለሚገኙ የኤሌክትሪክ መገልገያ እቃዎች ስሪትም አሸዋ ግብአት ነው።
ምንም እኳ ከሰሃራ እስከ አሪዞና ባሉ ሰፋፊ በርሃዎችና በባህር ዳርቻዎች ቢገኝም፤ በአቅራቢያ ከሚገኝ መደብር በቀላሉ ልንገዛው የምንችለው ነገር ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ዓለም ላይ የአሸዋ እጥረት አጋጥሟል።
ለመሆኑ በዓለም ላይ የትም ቦታ የሚገኝ ነገር እንዴት እጥረት ሊፈጠርበት ይችላል?
በዓመት 50 ቢሊዮን ቶን አሸዋ በሰዎች ጥቅም ላይ ይውላል። ይህ የአሸዋ መጠን መላዋን እንግሊዝ ሊያለብስ የሚችል ነው።
አጥኚዎቹ እንደሚሉት ችግሩ ያለው ጥቅም ላይ እየዋለ ባለው አሸዋ አይነት ምክንያት እንደሆነ እየተናገሩ ነው። ከላይ ለተጠቀሱት አገልግሎቶች ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው ለስላሳውና በቀላሉ በንፋስ የሚበነው የበረሃ አሸዋ አይደለም።

የፎቶው ባለመብት, Michel BARET
ይህ በጣም ደቃቅ የበረሃ አሸዋ ለኮንክሪት የሚሆን አይደለም። ይልቁንም ለሰዎች አስፈላጊ የሆነው ባለ ማእዘኑ እና በወንዞች እና በሃይቆች የሚገኘው ነው። ስለዚህም ይህኛውን አሸዋ ለማግኘት በወንዞች መድረሻ፣ በእርሻ ማሳዎ እንዲሁም በጫካዎች ውስጥ ሕገ ወጥ ፍለጋ ይካሄዳል።
ጥቂት በማይባሉ አገራትም የወንጀለኛ ቡድኖች በዚህ የአሸዋ ንግድ ላይ ተሰማርተዋል፤ በዚህ ሳቢያ ደግሞ የአሸዋ ጥቁር ገበያም ተስፋፍቷል።
"የአሸዋ እጥረት ጉዳይ ብዙዎች እያስገረመ ነው ግን ሊያስገርም አይገባም። ያለ ምንም አካባቢያዊ ተፅዕኖ የአንድን ተፈጥሯዊ ሃብት 50 ቢሊዮን ቶን የሚያክል ነገር ማውጣት የሚቻል ነገር አይደለም" ይላሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም ተመራማሪው ፓስካል ፔዱዚ።













