አሸዋ የሰረቁ ፈረንሳያውያን ጥንዶች ለእስር ተዳረጉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
40 ኪሎ ግራም አሽዋ ሰርቀዋል ተብለው የተጠረጠሩት ፈረንሳያውያን ጥንዶች ቢያንስ የስድስት ዓመት እስራት ይጠብቃቸዋል ተባለ።
ጥንዶቹ በሜዲትራኒያን ባህር ላይ ከሚገኑ ደሴቶች አንዷ ከሆነችው ሰርዲኒያ ደሴት ወስደዋል የተባለው 40 ኪሎ ግራም አሸዋ መኪናቸው ውስጥ ተገኝቷል።
ለጉብኝት ወደስፍራው ያቀኑት ጥንዶቹ አሸዋውን የወሰድነው "እንደ ማስታወሻ" እንዲሆነን እንጂ አሸዋ መውሰድ ወንጀል እንደሆነ እያወቅን አይደለም ብለው ተከራክረዋል።
ዝና ገናናው የሰርዲኒያው ነጭ አሸዋ እንደ ህዝብ ንብረት የሚቆጠር ሲሆን ከደሴቱ ላይ መውሰድም የተከለከለ ነው።
የደሴቷ ነዋሪዎች አሸዋውን ጨምሮ ሌሎች ንብረቶቻችን እየተዘረፉብን ነው ሲሉ በተደጋጋሚ ቅሬታቸውን ያሰሙ ነበር።
ከሰርዲኒያ ደሴት ላይ ዛጎሎች፣ ልዩ ጠጠሮች እና አሸዋ መውሰድ ወንጀል ተደርጎ ከሁለት ዓመት በፊት በህግ ከ1-7 ዓመት የሚያስቀጣ ሕግ ሆኖ ተቀምጧል።
ሁለቱ ፈንሳያውያን በአሸዋ ከተሞሉ 14 ፕላሰቲክ ጠርሙሶች ጋር በቁጥጥር ሥር የዋሉት ከሰርዲኒያ ደሴት ወደ ፈንረንሳይ የሚወስዳቸው መርከብን ከተሳፈሩ በኋላ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Sardegna rubata e depredata
የደሴቷ ባለስልጣናት በየዓመቱ ከደሴቷ ብዙ ቶን አሽዋ እየተሰረቀ መሆኑ እጅጉን አሳስቧቸዋል።
"አሽዋማ የባህር ዳርቻዎች የደሴቷ መስህብ ናቸው። የደሴቷ አሸዋ እየተሸረሸረ እና በስርቆት እየቀነሰ ነው። " ሲሉ የደሴቷ ነዋሪ እና የተፈጥሮ ሃብት ተመራማሪው ፒአረሉጊ ኮኮ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አውሮፓውያን ጉብኚዎች በተለይ ደግሞ ጣሊያናዊያን ከደሴቷ አሸዋ ከወሰዱ በኋላ በግብይት ድረ-ገጾች ላይ ለጨረታ በከፍተኛ ገንዘብ ይሸጣሉ።












