በሱዳን በፋብሪካ ላይ በተፈጠረ የእሳት አደጋ የሟቾች ቁጥር 23 ደረሰ

በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም በአንድ የሴራሚክ ማምረቻ ፋብሪካ በተከሰተ ፍንዳታ እና የእሳት አደጋ ቢያንስ 23 ሰዎች ሲሞቱ ከ130 በላይ ሰዎች ለጉዳት መዳረጋቸውን የአገሪቱ መንግሥት አስታወቀ።

የእሳት አደጋው የጋዝ ታንከር በመፈንዳቱ የተከሰተ እንደሆነ ታውቋል።

ሕንፃው በእሳት ከመያያዙ አስቀድሞም ከባድ ፍንዳታ መሰማቱ ተገልጿል።

"የፍንዳታው ድምፅ ከባድ ነበር፤ በግቢው ውስጥ ቆመው የነበሩ በርካታ መኪኖችም በእሳት ተያይዘዋል" ሲል የፋብሪካው ሠራተኛ የሆነ ግለሰብ የተመለከተውን ለኤ ኤፍ ፒ ተናግሯል።

በፋብሪካው ውስጥ ሌሎች በትክክል ያልተቀመጡ ተቀጣጣይ ነገሮች በመኖራቸው እሳቱ በቀላሉ እንዲዛመት ምክንያት መሆኑንም ኤ ኤፍ ፒ የዜና ወኪል ዘግቧል።

የእሳት አደጋ ሠራተኞች በሥፍራው ከመድረሳቸው በፊትም የእሳት ነበልባልና በጣም የጠቆረ ጭስ በሰማዩ ላይ ተስተውሏል።

የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ተጎጂዎችን እና የሟቾችን አስክሬን እያወጡ ሲሆን ሌሎቹን ለመታደግ ፍለጋ ላይ ተሰማርተዋል።

አደጋውን የአገሪቷ የቴሌቪዥ ጣቢያ "ከባድ የሆነ የሰው እና ንብረት ጥፋት" ሲል ገልፆታል።