ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቱርክ የፈረንሳዩን ፕሬዝደንት 'ሽብርን ይደግፋሉ' ስትል ከሰሰች
የቱርኩ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር፤ የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን ሽብርተኝነትን ይደግፋሉ ሲሉ ተቹ።
የፈረንሳይ ባለስልጣናት ቱርክ በሶሪያ የወሰደችውን እርምጃ መተቸታቸውን ተከትሎ ነው የቱርኩ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ሜቭሉት ካቩሶግሉ ይህን ትችት የሰነዘሩት።
የውጪ ጉዳይ ሚንስትሩ ማክሮን የአውሮፓ መሪ መሆን ቢፈልጉም፤ መረጋጋት እንኳ አልቻሉም በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ባለፈው ወር ማክሮን በኩርዶች የሚመሩትን የሶሪያ ዲሞክራቲክ ኃይል ተቀብለው ማነጋገራቸው ቱርክን እጅጉን አበሳጭቶ እንደነበረ ይታወሳል።
የፕሬዝደንት ማክሮን ጽ/ቤት የሶሪያ ዲሞክራቲክ ኃይልን ተቀብለው ያነጋገሩት አይኤስን በመዋጋት ረገድ ለሚያሳዩት አጋርነት እውቅና ለመስጠት እና ቱርክ በሰሜን ሶሪያ ላይ ልትወስደው ስላሰበችው የጦር እርምጃ ለመምክር መሆኑን አስታውቆ ነበር።
ኩርዶች በቱርክ፣ ኢራቅ፣ ኢራን እና ሶሪያ ውስጥ ተበታትነው የሚኖሩ ሲሆን፤ የራሳቸውን ሉዓላዊት፣ ነጻ አገር ለመመስረት ይታገላሉ።
በቱርክ ብቻ ወደ 20 ሚሊዮን የሚጠጉ ኩርዶች እንደሚኖሩ የሚገመት ሲሆን፤ ቱርክ ነጻ አገርን ለመመስረት የሚታገሉትን ኩርዶች አሸባሪ ስትል ትፈርጃቸዋለች።
የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን ከሦስት ሳምንታት በፊት ባደረጉት ንግግር የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ቱርክ በሰሜን ሶሪያ ለጀመረችው ወታደራዊ እርምጃ ምላሽ መስጠት ባለመቻሉ ክፉኛ ኮንነውታል።
ማክሮን ኔቶን "አዕምሮው ሞቷል" ሲሉም ገልጸውታል።
በተጨማሪም የኔቶ አባል አገራት ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረግ እና ከውሳኔ መድረስ እንደተሳናቸው ተናግረዋል።
የቱርኩ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ሜቭሉት ካቩሶግሉ፤ ትናንት ከአገሪቱ የሕዝብ እንደራሴዎች ፊት ቀርበው፤ "እሱ [ማክሮን] የአሸባሪ ደጋፊ ነው። በተደጋጋሚ ወደ ቤተ-መንግሥት እየጠራ ያስተናግዳቸዋል። ወዳጆቼ አሸባሪ ኃይሎች ናቸው ካለ ከዚህ በላይ ምንም ማለት አይቻልም" ብለዋል።
ቱርክ ወደ ሰሜን ሶሪያ ዘልቃ በመግባት "ደህንነቱ የተረጋገጠ ቀጠና" ለመፍጠር ከ30 በላይ ኪሎ ሜትሮችን ዘልቃ በመግባት የጦር እርምጃዎችን ስትወስድ ቆይታለች።
በዚሁ ቀጠና የቱርክ እና ሩሲያ ጥምር ኃይል የምድር ቅኝት እያደረጉ ይገኛሉ።
ቱርክ ከወራት በፊት ዘመናዊ ሩሲያ ሰራሽ ኤስ-400 የተሰኙ ከምድር ወደ አየር ሚሳኤል ሥርዓቶችን ከክሬምሊን መግዛቷን ተከትሎ ከኔቶ አባል አገራት ጋር ያላት ወዳጅነት ሻክሯል።