የሁቲ አማጽያን፡ ቪዲዮው በሳዑዲ ጦር ላይ አስመዘገብን ያሉትን ድል አያሳይም ተባለ

የሁቲ አማጺያን በየምን ሰነዓ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የሁቲ አማፂያን በርካታ የሳዑዲ ወታደሮችን መማረካቸውን አስታውቀዋል

በየመን የሚገኙ የሁቲ አማጺያን በሁለቱ አገራት ድንበር አቅራቢያ የፈፀሙትን ድብደባ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል አውጥተዋል።

ባሳለፍነው ቅዳሜ የሁቲ ቃል አቀባይ እንዳሉት የሳዑዲ አረቢያን የጦር ብርጌድ በሳዑዲዋ ከተማ ናጅራን አቅራቢያ መማረካቸውን አስታውቀዋል። ይሁን እንጅ ሳዑዲ አረቢያ ስለጉዳዩ የሰጠችው አስተያየት የለም።

ተንቀሳቃሽ ምስሉ በጦር መኪና ላይ ጥቃት ሲፈፀም የሚያሳይ ቢሆንም ግን 'ማርኬያቸዋለሁ' ስላላቸው የጦር ብርጌድ ምስሉ የሚያሳየው አንዳችም ነገር የለም።

ኮሎኔል ያህያ ሳሬል ቅዳሜ እለት "የሳዑዲ ወታደሮችን አሳራቸውን አብለተናቸዋል፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቿን ጨምሮ በሕይወትና በመሣሪያዎች ላይ ከባድ ጥፋት አድርሰናል" ብለው ነበር።

በመሆኑም የተቀረፁት ምስሎች በሁቲ ረን አል ማሲራህ ቴሌቪዥን ኔትወርክ እንዲታይ ይደረጋል ብለዋል።

ነገር ግን ትናንት የተላለፈው ተንቀሳቃሽ ምስል አማጺያኑ በመንገድ ላይ ያሉ ተሸከርካሪዎችን ሲያቃጥሉ ብቻ የሚያሳይ ነበር።

የተቃጠሉ በርካታ ተሸከርካሪዎች ምስልም ተከታትለው ታይተዋል። በተጨማሪም መሣሪያ የያዙ ነገር ግን የወታደር መለያ ልብስ ያልለበሱ ሰዎች በቡድን ሆነው መንገድ ላይ ሲጨፍሩ የሚያሳይ ነበር።- ምስሉ።

ታዲያ ኮሎኔሉ ትናንት በሰጡት መግለጫ 'አስመዝገበናል' ያሉትን ድል የሚያሳየው ተንቀሳቃሽ ምስል መቼ እንደሚታይ ቀኑን በግልፅ ያልተናገሩ ሲሆን

ለደህንነት ሲባል ተንቀሳቃሽ ምስሉ እንደማይተላለፍ ተናግረዋል።

በኢራን የሚደገፈው ሁቲ እንዳለው ከሆነ ባሳለፍነው ሳምንት በሳዑዲ የነዳጅ ማደያ ላይ በሰው አልባ የጦር አውሮፕላንና ሚሳኤል በመጠቀም ጥቃት ፈፅመዋል። ይህም የዓለም የነዳጅ ገበያ ላይ ተፅዕኖ እንዳሳደረ ገልፀዋል።

በአሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ እና ጀርመን የሚደገፈው የሳዑዲ ጦር ለጥቃቱ ኢራን ጥፋተኛ ናት ሲሉ ቢከሱም ቴህራን በበኩሏ እኔ የለሁበትም ብላለች።

የመን

የመን በጎርጎሳውያኑ 2015 ፕሬዚደንት አብድራቡህ ማንሶር ሃዲ እና የምክርቤት አባላቶቻቸው ዋና መዲናዋን ሰነዓን ጥለው እንዲወጡ በሁቲ አማጺያን ከተገደዱ ጀምሮ የጦር አውድማ ሆናለች።

የሁቲ አማጺያንም የአገሪቷን ሰሜናዊ ክፍል ተቆጣጥሮታል።

ከዚያም ሳዑዲ አረቢያ ፕሬዚደንቱ እንዲመለሱና ጥምረት በመፍጠር በሁቲ አማጺያን ላይ ድብደባ እየፈፀሙ ይገኛሉ።

ጥምረቱ በየቀኑ የአየር ድብደባ ይፈፅማል። የሁቲ አማጺያንም አፀፋውን በሳዑዲ ላይ ሚሳኤል በመተኮስ ይመልሳል።

ይሄው የርስ በርስ ጦርነት በዓለማችን አስከፊ የሆነውን የሰብዓዊ ቀውስ አስከትሏል።

80 በመቶ ከሚሆነው የየመን ነዋሪ ነፍሳቸውን ለማቆየት የምግብ እርዳታ የሚደረግላቸውን 10 ሚሊየን ሰዎች ጨምሮ 24 ሚሊየን የሚሆኑት ጥበቃና ሰብዓዊ እርዳታ ይፈልጋሉ።

እንደ የተባበሩት መንግሥታት ከሆነ ከአውሮፓዊያኑ 2016 ጀምሮ በግጭቱ ከ70 ሺህ የሚበልጡ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።